“በክልሉ የተከሰተዉ የጸጥታ ችግር የቱሪዝም ዘርፉን አዳክሞታል” አየለ አናውጤ (ዶ.ር)

25

ባሕር ዳር: ሰኔ 24/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ ከተጠሪ ተቋማት እና ባለድርሻ አካላት ጋር በመኾን በ2016 በጀት ዓመት እቅድ አፈጻጸም ዙሪያ ውይይት አካሂዷል።

ባለፉት ዓመታት በዓለም እና በሀገር አቀፍ ደረጃ ተከስቶ የነበረው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ፣ በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ተከስቶ የነበረው ጦርነት እንዲሁም አሁን ላይ ደግሞ በክልሉ የተከሰተው የጸጥታ ችግር የቱሪዝም ዘርፉን እያዳከመው መኾኑ በውይይቱ ተነስቷል።

የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኀላፊ አየለ አናውጤ (ዶ.ር) እንዳሉት በበጀት ዓመቱ ከተሠሩ ሥራዎች ውስጥ የቅርስ ጥበቃ እና እንክብካቤ ሥራ አንዱ ነው። ቢሮው በመደበው ከ74 ሚሊዮን ብር በላይ እና በማኅበረሰቡ ተሳትፎ የ85 ቅርሶች ጥገና ሥራ መሠራቱንም ነው የገለጹት።

ተቋርጦ የነበረውን የባሕል እና ኪነ ጥበብ ፌስቲቫል እና ውድድር በማካሄድ ዘርፉን የማነቃቃት ሥራ ተሠርቷል ብለዋል። ከ41 ሺህ በላይ ለሚኾኑ ዜጎችም በቋሚነት እና በጊዜያዊነት የሥራ እድል መፈጠሩንም ገልጸዋል።

ምክትል ኅላፊው እንዳሉት በበጀት ዓመቱ ይጎበኛሉ ተብሎ ከታቀደው 8 ነጥብ 1 ሚሊዮን የሀገር ውስጥ ጎብኝዎች ውስጥ 84 በመቶው ክልሉን ጎብኝተዋል።

ከዚህም 2 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ገቢ ተገኝቷል። ይጎበኛሉ ተብሎ ከታቀደው 93 ሺህ የውጭ ሀገር ጎብኝዎች ውስጥ ደግሞ 20 በመቶ የሚኾኑት ጎብኝተዋል። በዚህም 90 ሚሊዮን ብር ገቢም ተገኝቷል።

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ፣ የሰሜኑ ጦርነት አሁን ላይ ደግሞ በክልሉ የተከሰተው የጸጥታ ችግር ዘርፉን ማዳከሙን ገልጸዋል። በተለይም ደግሞ በዘርፉ ተሰማርተው የነበሩ አስጎብኝዎች ተበትነዋል፤ በዘርፉ ብቻ ጥገኛ የኾኑ ሆቴሎችም ሠራተኞቻቸውን መበተናቸውንም ገልጸዋል።

ባለፋት ዓመታት በቱሪዝሙ ዘርፍ ጉዳት ከደረሰባቸው ማኅበራት ውስጥ የዘጌ አካባቢ አስጎብኝዎች ማኅበር አንዱ ነው።

የማኅበሩ ሊቀመንበር ኃብተማርያም ጽጌ እንዳሉት ባለፉት ዓመታት ወጣቶች በማኅበር በመደራጀት በዘጌ ዙሪያ የሚገኙ ጥንታዊ ገዳማትን ሲያስጎበኙ ቆይተዋል። በሚያገኙት ገቢም ኑሯቸውን ሲመሩ ቆይተዋል።

ይሁን እንጂ በኮሮና ቫይረስ፣ በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት አሁን ላይ ደግሞ በክልሉ በተከሰተው የጸጥታ ችግር ምክንያት የጎብኝዎች በተለይም ደግሞ የውጭ ጎብኝዎች ቁጥር በመዳከሙ አስገብኝዎች ከሥራ ውጭ ኾነዋል። ቤተሰቦቻቸውም ለችግር መጋለጣቸውን ገልጸዋል።

አስጎብኝዎች ሀገርን በማስተዋወቅ ሚናቸው የጎላ በመኾኑ የተበተኑ ማኅበራትን በማሰባሰብ ማሠልጠን እና ወደ ሥራ መመለስ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleገበታ ለትውልድ የጎበኘው “የሎጎ ሐይቅ”
Next articleምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በጋምቤላ ክልል የሚገኘውን የአኮቦ ኢትኖ የማዕድን ኩባንያ ጎበኙ፡፡