
ባሕር ዳር: ሰኔ 24/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን የሚገኘው የሎጎ ሐይቅ በሰንሰለታማ ተራሮች የተዋበ ድንቅ ስፍራ ነው፡፡ የሐይቁ መልክዓ ምድራዊ ገጽታም ለዕይታ ማራኪ ነው
ከደሴ ከተማ በስተ ሰሜን አቅጣጫ በ30 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው ይህ ሥፍራ ከክልሉ ዋና ከተማ ባሕር ዳር በ470 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል።
በተሁለደሬ ወረዳ የሚገኘው ይህ ውብ የተፈጥሮ ሐይቅ ከባሕር ወለል በላይ 1 ሺህ 950 ሜትር ከፍታ ላይ ይገኛል። ስፋቱ 35 ስኩዌር ኪሎ ሜትር የሚሸፍን እና አማካይ ጥልቀቱ ደግሞ ከ23 እስከ 88 ሜትር እንደሚደርስ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡
የሎጎ ሐይቅ ለዕይታ ውብ እና ማራኪ ከመኾኑ ባሻገር ሐይቁ በዓሣ ምርት ይታወቃል። ቀረሶ፣ ዱቤ እና አምባዛ የተሰኙ የዓሣ ዝርያዎች በሐይቁ ይገኛሉ፡፡
የሎጎ ሐይቅ በዓሣ ማስገር ሥራ ለተሰማሩ ወጣቶችም የሥራ ዕድል በመፍጠር ብሎም ለኅብረተሰቡ የገቢ ምንጭ በመኾን እያገለገለ ይገኛል።
የሞተር ጀልባዎችን ጨምሮ ለጎብኚዎች የትራንስፖርት እና የመዝናኛ አገልግሎት የሚሰጡ ጀልባዎች አሉት። መለስተኛ ሎጅዎች፣ ሆቴሎች እና ካፍቴሪያዎችም በአካባቢው ስለሚገኙ ለጎብኚዎች ምቹ የቱሪዝም መዳረሻ ነው።
ይህ በመልክዓ ምድራዊ ገጽታው ውበትን የተላበሰው የሎጎ ሐይቅ በአሁኑ ወቅት ወደ መልማት ተሸጋግሯል።
የተደበቁ እና የቆዩ የአካባቢ ፀጋዎችን በማልማት እና ወደ ሃብት በመቀየር የቱሪዝም ዘርፉ በኢኮኖሚ ውስጥ የበኩሉን ሚና እንዲጫወት ለማድረግ ያለመው የ”ገበታ ለትውልድ” ሀገራዊ ፕሮጀክት ለሎጎ ሐይቅም የመልማት ዕድሉን ከፍቷል።
የሎጎ ሐይቅ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ.ር) ሃሳብ አመንጭነት በ”ገበታ ለትውልድ” ፕሮጀክት እየለማ ይገኛል።
ወሎ እና አካባቢውን የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ ታስቦ እየለማ የሚገኘው ይህ ፕሮጀክት በአሁኑ ወቅት ሰፊ የሥራ ዕድል እየፈጠረ ይገኛል።
በደቡብ ወሎ ዞን ሦስት የተለያዩ የተፈጥሮ ሐይቆች ይገኛሉ። በስፋት ትልቁ ሎጎ ሐይቅ ነው። ሌሎቹ ሁለቱ የተፈጥሮ ሐይቆች አርዲቦ እና ማይባር ይባላሉ። ሎጎ እና አርዲቦ ሐይቆች መገኛቸው ተሁለደሬ ወረዳ ነውተ ማይባር ሐይቅ ደግሞ በአልብኮ ወረዳ ይገኛል።
አርዲቦ ከሐይቅ ከተማ በስተምሥራቅ 15 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል። ማይባር ሐይቅ ከደሴ ከተማ በስተደቡብ 23 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ እንደሚገኝ ከደቡብ ወሎ ዞን የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!