
ባሕር ዳር: ሰኔ 24/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የምንኖርበት ዓለም በአንድ ጊዜ በርካታ መረጃዎችን ማግኘት የምንችልበት ነው።
አንድ ጊዜ ተንቀሳቃሽ ስልካችንን አለያም ኮምፒውተራችንን ከከፈትን ማባሪያ በሌለው መንገድ ዜናዎች፣ ጹሑፎች እና የማኀበራዊ ሚዲያ መልዕክቶችን እናገኛለን። እነዚህ መረጃዎችም የእኛን ትኩረት ለመሳብ ይሽቀዳደማሉ።
በዚህ የመረጃ ውቅያኖስ ውስጥ ግዙፍ አደጋ ተደቅኗል ይኸውም የመረጃ ብክለት ነው።
በእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት እና ሥነ ተግባቦት መምህር አየለ አዲስ (ዶ.ር) የተሳሳቱ መረጃዎች በተለያየ መንገድ ተዘጋጅተው ሲቀርቡ የመረጃ ብክለትን እንደሚያስከትሉ ያብራራሉ። እንደ እሳቸው ገለጻ በርካታ ዓይነት የመረጃ ብክለት መንገዶች አሉ።
👉 ኾን ተብሎ የሚዘጋጁ ሃሰተኛ መረጃዎች (መረጃውን ያዘጋጀው ሰው ሀሰተኛ መኾኑን እያወቀ ኾን ብሎ የተሳሳተ መረጃ ሲያዘጋጅ እና ሲያሰራጭ) የሚፈጠር ነው።
👉 ሀሰተኛ መኾኑ ሳይታወቅ የሚሰራጭ መረጃ (ይህ ሰዎች ባለማወቅ የተሳሳተውን መረጃ ይጠቅማል ብለው በማሰብ ለሌሎች ሲያጋሩት) የሚፈጠር የመረጃ ብክለት ነው።
👉 በእውነተኛ መረጃ ላይ ተመስርቶ ጎጅ መረጃዎችን ማሰራጨት (ይህ ደግሞ ጥቂት እውነታ ላይ ተመስርቶ ጎጅ እና የተሳሳቱ መረጃዎችን ማሰራጨት ነው) ይህም ኾን ተብሎ መረጃ ተቀባዮችን ባልተገባ እና በተሳሳተ መንገድ ለመምራት ታስቦ የሚደረግ ነው።
ዶክተር አየለ መረጃ የሚበከልበት መንገድ ብዙ እና ውሥብሥብ ነው ይላሉ። ከተጠቀሱት ሦስቱ መንገዶች በተጨማሪም የጥላቻ ንግግር፣ የምፀት መረጃዎች፣ ሃሰተኛ የፈጠራ መልዕክቶች፣ ንግግሮችን ከአውድ ውጭ በማቅረብ፣ ሰዎችን ማሳሳት እና ሌሎች ከመረጃ ብክለት እንደሚመደቡ ያብራራሉ።
በርካታ ብዝኀነቶች ባሉባት ኢትዮጵያ የመረጃ ብክለት ሰፊ እና ውሥብሥብ ችግሮችን እንደሚያስከትል ዶክተር አየለ ተናግረዋል። ባለፉት ጥቂት ዓመታት በመረጃ ብክለት ምክንያት በኢትዮጵያ ንጹሐን ተገድለዋል፣ ንብረት ወድሟል፣ ቤተ እምነቶች ተቃጥለዋል፣ የሕዝቦች አብሮ የመኖር እሴት ተጎድቷል፣ የፖለቲካ አለመረጋጋት ተፈጥሯል እንዲሁም ሌሎች ማኀበራዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳቶች ደርሰዋል።
👉 የመረጃ ብክለት በማን ይፈጠራል?
ዶክተር አየለ አዲስ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀንን ጥናት በማጣቀስ እንዳብራሩት መረጃ የተለያየ ዓላማን ባነገቡ ሰዎች ይፈጠራል። የመጀመሪያዎቹ ትኩረትን ለማግኘት በማሰብ መረጃን በሚያሰራጩ ግለሰቦች ይፈጠራል። እነዚህ ግለሰቦች ትኩረት ለመሳብ ብቻ የተለያዩ ስሜት ቀስቃሽ መልዕክቶችን በመልቀቅ መረጃን ይበክላሉ።
ሁለተኛዎቹ ግለሰቦች ገንዘብ ለማግኘት የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች ናቸው። እነዚህ ደግሞ በርካታ ተከታይ በማግኘት ከማስታወቂያ ሽያጭ የሚያገኙትን ገንዘብ በማሰብ መረጃን የሚበክሉ ናቸው።
ሌሎች መረጃ ብክለት ላይ አስተዋጽኦ ያላቸው የማኅበረሰብ አንቂዎች ናቸው። እነዚህ ደግሞ የራሳቸውን ቡድን ፈጥረው የራሳቸውን አመለካከት በታዳሚያን ላይ ለመጫን የሚሠሩ ናቸው።
ፖለቲከኞችም የመረጃ ብክለትን በመፍጠር የራሳቸውን አሉታዊ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ። የዘመኑ ፖለቲካ ከፊት ለፊት ንግግር ወጥቶ በማኀበራዊ ሚዲያ እየተደረገ በመኾኑ ፖለቲከኞች ሕዝብን በሃይማኖት እና ብሔር ለማሰለፍ በሚያደርጉት የፖለቲካ አሻጥር መረጃዎችን ይበክላሉ።
👉 የመረጃ ብክለትን እንዴት እንከላከል?
ዶክተር አየለ የተበከለ መረጃን በመከላከል ሂደት የግለሰቡ ኀላፊነት ከፍተኛ እንደኾነ ተናግረዋል። ማንኛውም ሰው ያገኘውን መረጃ ሁሉ ትክክል ነው ብሎ ማመን እንደሌለበት እና እውነታውን ማጣራት እንዳለበት መክረዋል። በተለይ እውነታን በማጣራት ሂደት ምንጩን መለየት አለበት፣ ስለ ገፁ ትክክለኛነት ማረጋገጥ፣ ከርዕሱ አልፎ ማንበብ፣ ጸሐፊውን በደንብ መለየት፣ አጋዥ ምንጮችን ማየት፣ ቀን እና ተያያዥ መረጃዎችን መለየት፣ ቀልድ (ቧልት) አለመኾኑን መለየት፣ የራሳችንን አድሎ ማጤን እንዲሁም ባለሙያዎችን መለየት ይገባል ነው ያሉት። ከዚህ በተጨማሪም ሌሎች የቴክኖሎጂ እውነት ማጣሪያ ዘዴዎችን መጠቀም እንደሚቻል ዶክተር አየለ አብራርተዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!