የሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን በሀገሪቱ ልማት እና ኢንቨስትመንት ለመሳተፍ ዝግጁ መኾናቸውን ገለጹ።

23

ባሕር ዳር: ሰኔ 24/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በተለያዩ ዓለም ሀገራት የሚኖሩ ሁለተኛ ትወልድ ኢትዮጵያውያን ክረምቱን ወደ ሀገራቸው በመግባት አሻራቸውን እንዲያኖሩ ጥሪ ማድረጋቸው ይታወሳል።

ይህን ተከትሎ ዛሬ በ26ኛው የሐረር ቀን በዓል ላይ ለመሳተፍ ከአውስትራሊያ እና አሜሪካ በርካታ ሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን አዲስ አበባ ገብተዋል።

ከእነዚህ ሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን መካከል በአውስትራሊያ ጠቅላላ ሀኪም የኾኑት ጀማል መሐመድ (ዶ.ር) በሙያቸው ሀገራቸውን ለማገልገል ዝግጁ መኾናቸውን ተናግረዋል።

የኩላሊት እጥበት ክሊኒክ ለማቋቋም ፕሮጀክት መቅረጻቸውንም አመልክተዋል። በተመሳሳይ ከአውስትራሊያ የመጡት ዱሴት አብዶሽ እና ፈቲሃ አብዱላሂ በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት ለመሳተፍ የረጅም ጊዜ እቅድ እንደነበራቸው አንስተዋል።

ወደ ሀገራቸው መግባታቸውን ተከትሎም በተለያየ የልማት እና ኢንቨስትመንት ሥራ ለመጀመር ዝግጁ መኾናቸውን ጠቁመዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ወቅቱ ትምህርት የሚዘጋበት በመኾኑ በርካታ ሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን ሀገራቸውን እንዲያውቁ ዕድል የሚሰጥ መኾኑንም ጠቅሰዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ መሠረት በሐረር ቀን በዓል ላይ ለመሳተፍ ወደ ኢትዮጵያ የመጡ ዜጎችን ኢንቨስትመንትን ጨምሮ በተለያዩ መስኮች ተሳትፏቸው እንዲጠናከር አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግ ተናግረዋል።

የሐረሪ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ምክትል ኅላፊ አብዱልሀኪም ዑመር የክልሉ ተወላጅ ዳያስፖራ አባላት የሐረር ቀን በዓልን ከማክበር ጎን ለጎን በተለያዩ በጎ አድራጎት መርሐ ግብሮች እንዲሳተፉ በክልሉ ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።

ነጻ የህክምና አገልግሎት፣ የትምህርት ቤት ቁሶች ድጋፍ እንዲሁም የአረንጓዴ አሻራን ጨምሮ የተለያዩ ተግባራትን እንደሚያከናውኑም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር በላይነህ አቅናው እንዳሉት ከዚህ ቀደም የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥሪ ተከትሎ በሁለት ዙር ሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን መጥተዋል።

አሻራዎን ያኑሩ በሚል መሪ ሀሳብ ከሰኔ 20/2016 ጀምሮ ባሉት ሦስት ወራት ሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን ሀገራቸውን እንዲያውቁ ለሦስተኛ ዙር ጥሪ መቅረቡንም ጠቁመዋል።

ኢዜአ እንደዘገበው ሀገራዊ ጥሪው ኢትዮጵያ ያለችበትን ተጨባጭ ሁኔታ በአካል ቀርቦ ለማየት እድል እንደሚሰጥም ነው ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ያነሱት።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ ሰላም እና መረጋጋት እንዲሰፍን አይተኬ ሚና ተጫውታለች” የምሥራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኀይል
Next article“መረጃን ሳያረጋግጡ መቀበል ብዙዎቹን ለጉዳት ዳርጓል” አየለ አዲስ (ዶ.ር)