
ባሕር ዳር: ሰኔ 24/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኀይል አባልነቷ በቀጣናው ሰላም እና መረጋጋት እንዲሰፍን አይተኬ ሚና መጫወቷን የምሥራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኀይል ገለጸ። በኬንያ ናይሮቢ ከሚገኘው የምሥራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኀይል ቢሮ የተውጣጣ ልዑክ ኢትዮጵያን ለምሥራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኀይል የምታዋጣውን ሞተራይዝድ ሻለቃ የግዳጅ ዝግጁነት የሚያረጋግጥ ቡድን ወደ ኢትዮጵያ ገብቷል።
ቡድኑ ዛሬ የቅድመ ዝግጁነት ማረጋገጥ እና ግምገማ መድረክ እያካሄደ ነው። የምሥራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኀይል ዳይሬክተር ብርጋዴር ጄኔራል ፖል ካሁሪያ ጀማ እና የኢፌዴሪ ጦር ኀይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ወታደራዊ አማካሪ እና የተኩስ አመራር ኀላፊ ሌተናል ጄኔራል ዓለምእሸት ደግፌን ጨምሮ የተጠባባቂ ኀይሉ መሪዎች እና ወታደራዊ መኮንኖች፣ የሲቪል ሥራ ኀላፊዎች እንዲሁም የአፍሪካ ኅብረት ተወካዮች ተገኝተዋል።
ብርጋዴር ጄኔራል ፖል ካሁሪያ ጀማ እንደገለጹት ኢትዮጵያ ለምሥራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኀይል ሙያዊነት የተላበሰ እና ብቁ ሠራዊት በማዋጣት አይተኬ ሚና እንደነበራት አንስተዋል። ኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍ አስተዋጽኦ በመወጣት የምትታወቅ ሀገር ስለመኾኗም ጠቅሰዋል። ለምሥራቅ አፍሪካ ሰላም እና መረጋጋት እንዲሰፍን ትልቅ ልምድ እና ተሞክሮ ያላት ሀገር መኾኗን ገልጸው፣ እስካሁንም ኢትዮጵያ በተሰማራችበት ተልዕኮ ሁሉ ለነበራት ወሳኝ አበርክቶ ምሥጋና አቅርበዋል።
በቀጣይም በቀጣናው ሀገራት ትብብርን በማጠናከር ዘላቂ ሰላም እና መረጋጋት እንዲሰፍን በቁርጠኝነት መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል። የጦር ኀይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ወታደራዊ አማካሪ እና የተኩስ አመራር ኀላፊ ሌተናል ጄኔራል ዓለምእሸት ደግፌ ኢትዮጵያ ምንጊዜም ለአፍሪካ እና ለቀጣናው ሰላም እና ፀጥታ በትብብር በመሥራት ቁልፍ ሚና የምትጫወት ሀገር መኾኗን ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ ለተጠባባቂ ኀይሉ እንደ መሥራች ሀገር በእስካሁን ታሪኳ ሃሳብ አመንጪነት ብቻ ሳይኾን በተግባር ግንባር ቀደም ተዋናይ ኾና እንደምትቀጥል ተናግረዋል። ኢትዮጵያ በፋይናንስ ረገድም ትልቅ በጀት መድባ ለቀጣናው ሰላም መስፈን እንደሠራችም ጠቅሰዋል። የተጠባባቂ ኀይሉ አቅም እንዲጠናከር ሁሉን አቀፍ ዝግጁነት እንዲኖረው እና ተልዕኮውን በብቃት እንዲወጣ ኢትዮጵያ ያላትን ቁርጠኝነት እና ዝግጁነት አንስተዋል።
የቀጣናው ሀገራት በሁሉም ዘርፎች ትብብር ማድረጋቸው ተጠባባቂ ኀይሉ ሰላም እና መረጋጋት እንዲሰፍን ሚናውን እንዲወጣ ትልቅ ሚና እንዳለው ጠቅሰው በዚህም የኢትዮጵያ ሞተራይዝድ ሻለቃ ሁልጊዜም ዝግጁ እንደኾነ ገልጸዋል። በቀጣናው የተሻለ ነገ እንዲመጣ እና ሰላም እና ብልጽግና እንዲረጋገጥ የነበረውን አይተኬ ሚና አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።
ኢዜአ እንደዘገበው የተጠባባቂ ኀይሉ ልዑክ በኢትዮጵያ ቆይታው የኢትዮጵያን የምሥራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኀይል ሞተራይዝድ ሻለቃ ጠቅላይ ጦር ሰፈር ተገኝቶ የሻለቃውን ዝግጅት እና ቁመና እንደሚመለከትም ይጠበቃል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!