አዲሱ የጋራ ገቢዎች ክፍፍል የክልሎችን ገቢ እንደጨመረ ተገለጸ፡፡

52

ባሕር ዳር: ሰኔ 24/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በኢፌዴሪ ፌዴሬሽን ምክር ቤት የድጎማ በጀት እና የጋራ ገቢዎች ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ጸሐፊ ኃይሉ ኢፋ የ2016 በጀት ዓመት ሪፖርቱን ባቀረቡበት ወቅት አዲሱ የጋራ ገቢዎች ቀመር ከ2013 በጀት ዓመት ጀምሮ የክልሎችን ገቢ የጨመረ መኾኑን ጠቅሰዋል፡፡

👉በ2013 በጀት ዓመት 22 ነጥብ 55 ቢሊዮን ብር
👉በ2014 በጀት ዓመት 34 ነጥብ 69 ቢሊዮን ብር
👉በ2015 በጀት ዓመት 48 ነጥብ 56 ቢሊዮን ብር እና
👉በ2016 በጀት ዓመት 11 ወራት 56 ነጥብ 34 ቢሊዮን ብር በቀመሩ መሠረት ለክልሎች እንዲተላለፍ መደረጉን ነው የተናገሩት፡፡

በ2016 በጀት ዓመት 11 ወራት 44 ነጥብ 08 ቢሊዮን ብር ትልልፍ ከባለፈው ዓመት የክልሎች ድርሻ ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ12 ነጥብ 26 ቢሊዮን ብር ዕድገት አሳይቷል ብለዋል። ይህም 27 ነጥብ 80 በመቶ እንደኾነ ነው የተገለጸው፡፡ አቶ ኃይሉ ኢፋ እንደተናገሩት የድጎማ በጀት እና የጋራ ገቢዎች አሥተዳደርን አስመልክቶ የማከፋፈያ ቀመሮቻቸው ቋሚ ኮሚቴው በዋናነት ያተኮረባቸው መሠረታዊ ጉዳዮች አብራርተዋል፡፡

አተገባበርን መከታተል እና መደገፍ፣ የፌዴራል መሠረተ ልማት ሥርጭት ፍትሐዊነትን ለማረጋገጥ በተዘረጋው የአሠራር ሥርዓት መሠረት ስለመፈፀሙ ክትትል እና ድጋፍ ማድረግ፣ ልዩ ዓላማ ያላቸው የፌዴራል ድጎማዎች ግልፀኝነት፣ ተጠያቂነት እና ዘላቂነት ባለው መልኩ በፍትሐዊነት ለክልሎች መከፋፈሉን ክትትል እና ድጋፍ ማድረግ፣ ተያያዥ መረጃዎችን መሠብሠብ እና ማደራጀት ቋሚ ኮሚቴው በዋናነት ያተኮረባቸው መሠረታዊ ጉዳዮች ነበሩ ብለዋል፡፡

አቶ ኃይሉ የጋራ ገቢዎች ቀመር አካል የኾነው የሮያሊቲ አሠባሠብ እና ትልልፍ እንደ ሌሎች የጋራ ገቢ ከጊዜ ወደ ጊዜ ጭማሪ እያሳየ ስለኾነ የክልሎችን ገቢ በመጨመር ረገድ አስተዋጽኦ ያለው ሲኾን፡-

✍️በ2013 የበጀት ዓመት ከዘርፉ 43 ነጥብ 92 ሚሊዮን ብር
✍️በ2014 የበጀት ዓመት 87 ነጥብ 82 ሚሊዮን ብር
✍️በ2015 የበጀት ዓመት 175 ነጥብ 53 ሚሊዮን ብር እና
✍️በ2016 የበጀት ዓመት የ10 ወር 349 ነጥብ 53 ሚሊዮን ብር ተሠብሥቦ በቀመሩ መሠረት መከፋፈሉን አስታውቀዋል፡፡

በከፍተኛ ማዕድን ዘርፍ ያለው አፈጻጸምም ከሌሎች የጋራ ገቢ አፈጻጸም አንጻር ሲታይ አሁንም ችግሮች ያሉበት ስለኾነ የፌዴራል እና የክልሎች ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው መሥራት እንደሚገባቸው ጨምረው ገልጸዋል፡፡ በ2016 የበጀት ዓመት የተመደበው ጥቅል ዓላማ ያለው የድጎማ በጀት 214 ነጥብ 074 ቢሊዮን ብር እና ለዘላቂ የልማት ግቦች የተመደበው 14 ቢሊዮን ብር ሲኾን በድጎማ በጀት ማከፋፈያ ቀመሩ መሠረት መከፋፈሉን ተናግረዋል፡፡

በተደረገው ክትትል እና ድጋፍም በሁሉም የፌዴራል ተቋማት አማካኝነት 40 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር የውስን ዓላማ የድጎማ በጀት ለሁሉም ክልሎች መተላለፉን አስረድተዋል፡፡ የቋሚ ኮሚቴው ጸሐፊ ለድጎማ በጀት ቀመር ዝግጅት የሚያስፈልጉ መረጃዎችን በማደራጀት በኩል በተለይም በአዳዲስ ክልሎች ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራት፣ የጋራ ገቢዎች አሥተዳደር፣ ክፍፍል እና ትልልፍን ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ የፌዴራል እና የክልሎች የጋራ ፎረም ማጠናከር፣ የጋራ ገቢዎች እና የድጎማ በጀት ቀመር እንዲሁም በምክር ቤቱ በተዘረጉ የአሠራር ሥርዓቶች ላይ ተከታታይነት ያለው የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና መስጠት በቀጣይ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች መኾናቸውን አመላክተዋል፡፡

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር በቋሚ ኮሚቴው ሪፖርት ላይ ምክር ቤቱ በጥልቀት ከመከረበት በኋላ ሪፖርቱ እንዲፀድቅ ለምክር ቤቱ ባቀረቡት መሠረት ምክር ቤቱ የቀረበለትን ሪፖርት በሙሉ ድምጽ ማጽደቁን ከፌዴሬሽን ምክር ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“አራት የፈጠራ ውጤቶቸ ከኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ባለሥልጣን የፓተንት መብት ተሰጥቶኛል” የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት
Next article“ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ ሰላም እና መረጋጋት እንዲሰፍን አይተኬ ሚና ተጫውታለች” የምሥራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኀይል