
ባሕር ዳር: ሰኔ 24/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የኒውክሌር ቴክኖሎጂን ለሰላማዊ ዓላማ ለመጠቀም ባሉ አማራጮች ላይ ከቻይና ብሔራዊ የኒውክሌር ቴክኖሎጂ ኀላፊዎች ጋር መምከሩን የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ገልጿል። የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ.ር) ኢትዮጵያ የኒውክሌር ቴክኖሎጂን በጤና፣ በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ እንዲሁም በኀይል አማራጭ ዙርያ ለሰላማዊ ዓላማ ለመጠቀም ከዚህ በፊት ከሩሲያ ፌዴሬሽን ጋር የስምምነት ሰነድ መፈራረሟን ገልጸዋል፡፡
አሁን ላይ ደግሞ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከሩሲያ ፌደሬሽን ጋር በመተባበር እየሠራ መኾኑን ነው ያስገነዘቡት። ሚኒስትሩ በዘርፉ ውጤታማ ሥራ ለመሥራት የኒውክሌር ኢነርጂ አቅም ግንባታ ዘርፎች ላይ የሰው ሃብት ልማት ሥልጠና እና መሰል ጉዳዮች ላይ የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከቻይናው ኑክሌር ኮርፖሬሽን ጋር ለመሥራት ፍላጎት እንዳለው አስረድተዋል።
የቻይናው ኑክሌር ኮርፖሬሽን ተወካዮች እንደገለጹት ከአዲስ አበባ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የኒውክሌር ልህቀት ማዕከል አቅም ግንባታ ላይ እገዛ ለማድረግ ስምምነት ለመፈረም የመጀመሪያ ዙር ውይይት ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡ በኢትዮጵያ የሰው ሃብት ሥልጠና እና ሌሎችም የዘርፉ ሥራዎች ላይ መሥራት እንደሚፈልጉ ገልጸዋል። በሥራው አተገባበር ዙሪያ ቀጣይ ውይይቶች እንደሚካሄድ በውይይቱ ላይ መነሳቱን ከኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!