
ባሕር ዳር: ሰኔ 24/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በታች አርማጭሆ ወረዳ መንግሥት ያቀረበውን የሰላም ጥሪ ተከትሎ ለገቡ ኀይሎች የተሀድሶ ሥልጠና ተሰጥቷል፡፡ የሥልጠናው ዋና ዓላማ በግጭት ተሳታፊ የነበሩ እና የሰላም ጥሪውን የተቀበሉ ኀይሎችን የማሠልጠን እና ወደ ኅብረተሰቡ በመቀላቀል ወደ መደበኛ ሥራቸው እንዲመለሱ ማድረግ እንደኾነ ተገልጿል፡፡
የክልሉን ሰላም አስተማማኝ በማድረግ እንዲሁም የምህረት አዋጁን መሠረት በማድረግ ሰላምን መርጠው ለገቡ ተገቢውን የተሀድሶ ሥልጠና በመስጠት ወደ ኅብረተሰቡ ቀላቅሎ የሰላም እና የልማት ባለቤቶች እንዲኾኑ ማድረግ ነው ተብሏል፡፡ በሕገ ወጡ ቡድን ውስጥ የሚሳተፉ አካላት ወደ ሰላማዊ ሕይወት እንዲመለሱ እንዲሁም የክልሉን ሰላም እና ልማት ከሚያውኩ ሀሳቦች እና ድርጊቶች እንዲታቀቡ መሥራት እንደሚያስፈልግ ተገልጿል።
አሁን ላይ የተፈጠረውን አንፃራዊ ሰላም ወደ ተሟላ እና ዘላቂ ሰላም ለመቀየር የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡም የሥልጠናው ተሳታፊዎች መግለጻቸውን ከማዕከላዊ ጎንደር ዞን የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!