ሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው እየገቡ ነው፡፡

19

ባሕር ዳር: ሰኔ 24/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ለሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን ያቀረቡትን ጥሪ ተቀብለው በሦስተኛው ምዕራፍ ላይ ለመሳተፍ ወደ ሀገር ቤት ለመጡ ተጓዞች ይፋዊ የአቀባበል ሥነ ሥርዓት በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ተካሂዷል።

በአቀባበል ሥነ ሥርዓቱ ላይ የሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን ጥሪ ብሔራዊ ኮሚቴ ምክትል ሠብሣቢ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ እንዲሁም የሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን ጥሪ ብሔራዊ ኮሚቴ አስተባባሪ እና የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር በላይነህ አቅናውን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።

በወቅቱም አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ባስተላለፉት መልዕክት ጥሪውን ተከትሎ ባለፉት ሁለት ዙሮች ሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው በመምጣት ከታሪካቸው እና ባሕላቸው ጋር በሚያስተሳስሯቸው ልዩ ልዩ ተግባራት ላይ መሳተፋቸውን ገልጸዋል። በሦስተኛው እና የማጠቃለያው ምዕራፍ ላይ ለሚሳተፉ ተጓዦችም የዕረፍት ጊዜያቸውን የሚያጣጥሙባቸው እና አሻራቸውን የሚያሳርፉባቸው በርካታ ተግባራት መሰናዳታቸውን ጠቅሰዋል።

ዛሬ አቀባበል ከተደረገላቸው ሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን መካከል በሐረሪ ክልል በሚከበረው 26ኛው ‘የሐረር ቀን’ ላይ ለመሳተፍ የመጡ ተጓዦች እንደሚገኙበት ጠቅሰው በመላው ዓለም የሚኖሩ ሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያንም ወደ ሀገራቸው በመምጣት ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

የሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን ጥሪ ብሔራዊ ኮሚቴ አስተባባሪ እና የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር በላይነህ አቅናው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ለኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ተከታታይ ጥሪዎችን ማካሄዳቸውን አስታውሰዋል። ይህ ጥሪም ሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያንን መሠረት አድርጎ የተጠራው ጥሪ ሦስተኛ እና የማጠቃለያ ምዕራፍ መኾኑን ገልጸዋል።

ጥሪው ‘አሻራዎን ያኑሩ፤ የእረፍት ጊዜዎን ያጣጥሙ’ በሚል መሪ መልዕክት የሚካሄድ መኾኑንም ነው የጠቀሱት። ጥሪው በሚቆይባቸው ሦስት ወራትም በልዩ ልዩ የዓለም ክፍል የሚኖሩ እና የዕረፍት ጊዜያቸውን በሀገራቸው የሚያሳልፉ ሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን የሚያሳትፉ በርካታ መርሐ ግብሮች ከፌዴራል እስከ ክልል ድረስ ተዘጋጅተዋል ነዉ ያሉት።

የተዘጋጁ መርሐ ግብሮች ወጣቶቹን ከሀገራቸው ጋር የሚያስተሳስሩ እና በልዩ ልዩ የክረምት የበጎ አድራጎት ተግባራት ላይ እንዲሳተፉ የሚያደርጉ መኾናቸውንም ጠቅሰዋል። ዛሬ ከአውስትራሊያ እና ከአሜሪካ ለመጡ ሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ይፋዊ አቀባበል መደረጉም ተገልጿል። በቀጣይ ጊዜያትም አቀባበሉ እንደሚቀጥል ከኢትዮጵያ ዲያስፖራ አገልግሎት የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleኅብረተሰቡ ሞተር አልባ ትራንስፖርትን እንዲያዘወትር ተጠየቀ።
Next articleየፌዴሬሽን ምክር ቤት የቀረቡትን አጀንዳዎች መርምሮ በሙሉ ድምጽ በማጽደቅ ጉባኤውን ማካሄድ ጀመረ፡፡