ኅብረተሰቡ ሞተር አልባ ትራንስፖርትን እንዲያዘወትር ተጠየቀ።

71

ባሕር ዳር: ሰኔ 23/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የሞተር አልባ ትራንስፖርት የማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓት በርካታ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በባሕር ዳር ከተማ ይፋ ኾኗል። የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ትራንስፖርት ጽሕፈት ቤት ከክልሉ ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ባለሥልጣን ጋር በመተባበር ባለድርሻ አካላት በተሳተፉበት የሞተር አልባ ትራንስፖርት የማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓት ይፋ ኾኗል። በሥነ ሥርዓቱ የተገኙት የአማራ ክልል ትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ዘውዱ ማለደ እንዳሉት ኅብረተሰቡ ሞተር አልባ ትራንስፖርትን በመጠቀም ምጣኔ ሀብታዊ፣ ማኅበራዊ ፣ ፖለቲካዊ እና ከባቢያዊ ጥቅሞችን ማግኘት ያስችለዋል ነው ያሉት።

ዋና ዳይሬክተሩ እንደ አብነት ያነሱት ባሕር ዳር ከተማ ውስጥ አንድ ግለሰብ አውቶቡስ በመጠባበቅ ከ10 እስከ 65 ደቂቃ በማባከን ዘርፈ ብዙ ኪሳራ ይገጥመዋል ሲሉ ተናግረዋል። ይሁንና ይህ ግለሰብ ብስክሌት ቢጠቀም ጊዜን፣ ገንዘብን፣ ሥራን እና ተልዕኮን በአግባቡ ማከናዎን ይገባዋል ብለዋል።

በክልሉ በአንድ ዓመት ብቻ በደረሰ የትራፊክ አደጋ የ315 የሰው ሕይዎት ተቀጥፏል፤ 53 ነጥብ 5 ሚሊዮን የሚገመት ንብረት ወድሟል ብለዋል። ታዲያ ሞተር አልባ ትራንስፖርትን መጠቀም ይህን መሰሉን ኪሳራ ለመቀነስ ያስችላል ነው ያሉት።

እንደ አቶ ዘውዱ ማብራሪያ መንግሥት ለዘርፉ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠትም በተለይ በባሕር ዳር ከተማ መንገድ ሲገነባ ብስክሌትን ታሳቢ ተደርጎ ነው ብለዋል። በመኾኑም ማኅበረሰቡ ሞተር አልባ ትራንስፖርትን በመጠቀም ጤናውን ፣ገንዘቡን፣ ጉልበቱን፣ ተፈጥሮን በመታደግ እንዲሁም ሥራን ሳይበድል አእምሮውን እያዝናና ዘርፈ ብዙ ተጠቃሚ ሊኾን ይገባዋል በማለት አብራርተዋል።

የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ አስሜ ብርሌ በበኩላቸው እንደ ሀገር ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ የሞተር አልባ ትራንስፖርት አገልግሎት ስትራቴጂክ ተቀይሶ ወደ ሥራ መገባቱን አስታውሰዋል። በባሕር ዳር በመንታ መንገድ ደረጃ 59 ኪሎ ሜትር ያህል የብስክሌት ምቹ መንገድ አለ ብለዋል። ምክትል ከንቲባው 85 ኪሎ ሜትር ገደማ ደግሞ የእግረኛ መንገድ በመኖሩ ኅብረተሰቡ ሲሻ በእግሩ ወይም ብስክሌት በመጠቀም ራሱን እያዝናና የበርካታ ጥቅሞች ተቋዳሽ መኾን ይችላል ነው ያሉት።

“አሁን በከተማዋ እየተገነባ ያለው 22 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት ብስክሌትንም ታሳቢ ያደረገነው” ያሉት አቶ አስሜ በቀጣይ ከተማ አሥተደደሩ ሞተር አልባ ትራንስፖርትን ለማስፋፋት በንቅናቄ እንደሚሠራም ጠቁመዋል።
በባሕር ዳር ከተማ ትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ባለሥልጣን የሞተር አልባ ትራንስፖርት ተወካይ አሥተባባሪ ደመላሽ ዘውዱ “ሞተር አልባ ትራንስፖርት አማራጭ ሳይኾን ዋነኛ የትራንስፖርት ዘርፍ ለማድረግ በዕቅድ እና ስትራቴጅ መሥራት ግድ ይላል” ብለዋል። የዓለም ሀገራት ወደዚህ ዘርፍ በከፍተኛ ሁኔታ መግባታቸው በመጠቆም።

ተወካይ አሥተባባሪው ጨምረው እንዳሉት ዛሬ በባሕር ዳር በይፋ የተጀመረው ሥነ ሥርዓት ክልሉን የሞተር አልባ ትራንስፖርት ስትራቴጅ እንዲኖረው የማድረጉ ሂደት አንዱ አካል ነውም ብለዋል። ከዓይነ ሥውራን ማኅበር የተወከሉት ዳንኤል አበበ በበኩልቸው ለሞተር አልባ ትራንስፖርት ምቹ መሠረተ ልማት ሲሠራ አካል ጉዳተኞችንም ታሳቢ እንዲደረግ ጠይቀዋል። በኮሪደር ልማቱ ምልክቶችን በቀለም ከመጠቆም ባለፈ ለዓይነ ሥውራን የመንገድ ዳር ኮሪደሮችን ከፍ በማድረግ ፣ የጎርፍ ማፋሰሻዎችን፣ የኤሌክትሪክ እና የስልክ ምሰሶዎችን እንዲሁም ሌሎች ለአካል ጉዳተኞች እንቅፋት የሚኾኑ ነገሮችን አስወግዶ መሥራት እንደሚገባም ጠቁመዋል።

በሙሉጌታ ሙጨ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleእኛ እና እንግሊዛውያን የተቸገሩ ዜጎችን የምንረዳበት መንገድ ለምን ተለያየ?
Next articleሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው እየገቡ ነው፡፡