
ባሕር ዳር: ሰኔ 23/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ በተለይ በትላልቅ ከተሞች ልመና በስፋት ይስተዋላል። እነዚህ እርዳታ ጠያቂዎች በተለያየ የዕድሜ፣ ፃታ፣ ዕምነት፣ አስተሳሰብ፣ ኢኮኖሚ እና ማኅበራዊ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ናቸው።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ለጋሽ ነው። ለእርዳታ እጁን ይዘረጋል። ሃይማኖተኛ ሕዝብ ስለኾነ የሚሰጠው ምፅዋት ፈጣሪውን እንደሚያስደስትለት ያምናል። ነገር ግን ለተመጽዋቹ የሰጠሁት ገንዘብ ለተመጽዋቹ አወንታዊ ነው ወይስ አሉታዊ አስተዋጽኦ ያለው የሚለውን የሚጠይቀው ሰው ቁጥሩ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም።
ዳቦ ግዛልኝ ላለች ታዳጊ ገንዘብ ከሰጠን በኃላ ዳቦ ትግዛበት አልያም ሌሎች መጥፎ ነገሮችን ታድርግበት አንከታተልም። ይህን ለመከታተል ጊዜም ላይኖረን ይችላል። ሁኔታውም ላይፈቅድልን ይችላል። ነገር ግን የሰጠነው ምጽዋት ከታዳጊዋ ላይ መጥፎ ተጽእኖ እንዲፈጥር አንፈልግም። ማወቅ ያለብን አንድ ትልቅ ቁምነገር ግን ሁሉም የሰጠነው ድጋፍ ተመጽዋቾችን አይጠቅምም። ስለዚህ የምንሰጠው ድጋፍ እንዴት የተመጽዋቾችን ሕይወት ሊቀይረው ይችላል? የምንሰጠው ድጋፍ እንዴት ተረጅዎችን በማይጎዳ መንገድ መኾን አለበት ብለን ማሰብ የሚኖርብን ይመስለኛል።
የዳቦ የለኝም፣ ርቦኛል፣ የማድርበት የለኝም፣ ወደ ሀገሬ ለመመለስ ገንዘብ አጣሁ የሚለውን የወገናችንን ሰቆቃ እየሰማን ምንም አለማድረግ የሚፈጥርብን የሥነ ልቦና ቀውስ አለ። እንደ አማኝነታችን ደግሞ ፈጣሪ ያየኛል ልንል እንችላለን። ነገር ግን እነዚህን እርዳታ ጠያቂዎች በተሻለ እና በዘላቂነት የምንደግፍበትን ዘዴስ አስበነው እናውቃለን? ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችስ እርዳታ ጠያቂዎችን በመደገፍ በኩል ምን ያሳያሉ? ልመና ኢትዮጵያ ብቻ አይደለም ያለው። ቁጥሩ እንደኛ የተጋነነ አይሁን እንጂ ልመና በሠለጠኑት የአውሮፓ እና ሰሜን አሜሪካ ሀገራትም አለ። በአንድ ወቅት ለትምህርት እንግሊዝ ሀገር በነበርኩበት ወቅት ለልመና ጎዳና ላይ ወጥተው የእርዱኝ ድምጽ ሲያሰሙ አይቻለሁ።
በእንግሊዝ ለመጀመሪያ ጊዜ እርዳታ ሲለመን ያየሁ ለንደን ከገባሁ ከሦስት ወር በኃላ ነበር። ይህን የተመለከትኩት ከእንግሊዛዊ ጎደኛየ አይዛክ ክሌሪ ጋር መሀል ለንደን እየተዝናናሁ ነበር። እርዳታ ጠያቂዋ በጎልማሳነት የእድሜ ደረጃ የምትገኝ ነች። “Help the homeless – መጠለያ የሌላቸውን እርዱ” የሚል ጽሑፍ እያሳየች ነው እርዳታ የምትጠይቅ። አልፎ አልፎ ብቻ ነው በአፏ እርዱኝ እያለች የምትጠይቀው እንጂ መልእክቷን በጉልህ ጽፋ በማሳየት ነው እርዳታዋን የምትጠይቀው።
እኔም ለንደን ላይ በዚህ ደረጃ ልመና ይኖራል ብየ ስላልገመትኩ በግርምት ነው የተመለከትኩት። የመዝናኛ ቀኔ ስለነበርም ጎደኛየ አይዛክ ክሌሪ ጋር በቅርብ ካለ ካፌ ተቀምጨ ከ1ሰዓት ያላነሰ ጊዜ የእርዳታ ጠያቂዋን እና የሕዝቡን ኹኔታ ተከታተልኩት። ዕውነት ለመናገር አንድም ሰው እርዳታ ሲሰጥ አላየኹም። እንግሊዛውያን እንዴት እርዳታ አይሰጡም ስል ለጎደኛየ አይዛክ ክሌሪ ጥያቄ አቀረብኩለት። የኢትዮጵያ ሕዝብ እርዳታ በመስጠት ያለውን ባሕልም አጋራሁት።
አይዛክ ክሌሪ እኛም እኮ እርዳታ እንሰጣለን። ስንሰጥ ግን ድጋፋችን ወደ ትክክለኛው እርዳታ ፈላጊ መሄዱን ማረጋገጥ እንፈልጋለን። ድጋፉም ተረጅዎችን የሚቀይር መኾኑን ማወቅ እንፈልጋለን። እኛ በግለሰብ ደረጃ የትኛው ነው እርዳታ የሚያስፈልገው የሚለውን ማወቅ ስለማንችል ይህን ኀላፊነት ለረጅ ድርጅቶች እንሰጣለን አለኝ።
ክሌሪ ሃሳቡን ቀጥሏል። ቤት አልባ ሰዎችን መደገፍ ከፈለግን የቤት አልባ ሰዎችን ችግር ለመቅረፍ የተቋቋመ ድርጅትን እንደግፋለን፣ በጦርነት የተጎዱ ሰዎችን ሕይወት ለመታደግ ከኾነ ይህንን የሚደግፉ ተቋማትን እንረዳለን፣ የአዕምሮ ህሙማንን ለመደገፍ ከፈለግን ከዚህ ላይ የሚሠሩ ድርጅቶችን እናግዛለን በማለት አብራራልኝ፡፡
እርግጥ ነው እንግሊዝ ሀገር ነገሮች ሁሉ ተቋማዊ ቅርጽ የያዙ ናቸው። ከጓደኛዬ አይዛክ ክሌሪ ሃሳብ በኃላ እኔም የእርዳታ ሥርዓታቸውን ማስተዋል ጀመርኩ። ልመናን የሚያስከትለው አንዱ እና ዋነኛው ምክንያት ድህነት ነው። እንግሊዛውያን ይህን ድህነት ወለድ ችግር ለመዋጋት በርካታ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችን መሥርተው ይንቀሳቀሳሉ። ከእነዚህ አንዱ ኦክስፋም ነው። በዚህ ድርጅት አማካኝነት ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ የዓለማችን ሀገራት ይረዳሉ።
ኦክስፋም ለእርዳታ የሚያውለውን ገንዘብ ከእንግሊዛውያን ይሠበሥባል። እንግሊዛውያን ኦክስፋምን ከሚደግፉበት መንገድ አንዱ የማይጠቀሙባቸውን ልብሶች፣ አንብበው የጨረሷቸውን መጽሐፍት እና ሌሎችን የማይጠቀሙባቸውን ቁሶች በመስጠት ነው። እንግሊዛዊው ጎደኛየ አይዛክ ክሌሪ ይህን እንደሚያደርግ ነግሮኛል።
ኦክስፋም እነዚህን ቁሶች ተረክቦ የሚሸጥባቸው ሱቆች ከፍቷል። በሽያጭ የተገኘው ገንዘብ ለኦክስፋም ከገባ በኃላ በእርዳታ መልኩ ወደ ተለያዩ ሀገራት ይሄዳል። ስለዚህ ድጋፉ እርዳታ የሚፈልጉ ሰዎችን በዘላቂነት በሚለውጥ መንገድ ይከናወናል።
ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ቅን ልቦች አሉ። ለመስጠት የተሰጡ ሰዎችም ብዙ ናቸው። ነገር ግን ይህን አቅም ችግረኞችን በዘላቂነት ለመደገፍ አልተጠቀምነውም። በየመንገዱ ዳር የምንሰጠው ድጋፍ ተጨማሪ እርዳታ ጠያቂዎችን ሲፈጥር እንጅ አወንታዊ ለውጥ ሲያመጣ እምብዛም አይስተዋልም።
እርዳታ የሚጠይቁ ሰዎች ራሳቸውን የሚችሉበት እና ሀገራቸውን የሚጠቅሙበት አቅም ውስጣቸው ላይ እንዳለ እንመን፤ ሁልጊዜም የእኛ ተመጽዋች እንዲኾኑ ሳይኾን በራሳቸው እንዲቆሙ እናግዛቸው። ለዚህ ደግሞ የእርዳታ አሰጣጥ ባሕላችንን ሥርዓታዊ እና ተቋማዊ እናድርገው እላለሁ። ሁሉም የእኔ ትዝብት ነው። እናንተ ደግሞ የሚሰማችሁን በአስተያየት መስጫ ሳጥኑ ላይ ልታስቀምጡ ትችላላችሁ። መልካም ጊዜ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!