“ዩኒቨርሲቲው ለጎረቤት ሀገራት የፖሊስ ሠራዊትና መኮንኖች የሚሰጠው የትምህርት ዕድል የሚያኮራ ነው” ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ

38

ባሕር ዳር: ሰኔ 22/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ የፖሊስ ሠራዊቱን በዕውቅትና ክህሎት ከማጎልበት ባለፈ ለጎረቤት ሀገራት እየሰጠ ያለው የትምህርት ዕድል ኢትዮጵያ ለቀጣናው ሰላም የምታበረክተው ጉልህ አስተዋጽኦ ማሳያ መኾኑን ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ መርሐ-ግብሮች ያሠለጠናቸውን የፖሊስ መኮንኖች አስመርቋል።

ዩኒቨርሲቲው ዛሬ ያስመረቃቸው የፖሊስ መኮንኖች በሁለተኛ ዲግሪ፣ በመጀመሪያ ድግሪ፣ በሌቭል አራት እና በጤና ሳይንስ እንዲሁም በሌሎች የትምህርት ዘርፎች የሰለጠኑ ናቸው።

ሠልጣኞች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ፖሊሳዊ ሳይንስ፣ ሥነ-ወንጀልና ወንጀል ፍትሕ እንዲሁም በፖሊስ መኮንንነት ዘርፍ አስፈላጊውን ሙያና ዕውቀት የጨበጡ መሆናቸው ተገልጿል።

ዩኒቨርሲቲው ዛሬ ካስመረቃቸው ሠልጣኞች መካከል ሲያሠለጥናቸው የቆዩ 12 የሶማሊያ እና የደቡብ ሱዳን የፖሊስ ሠልጣኞች ይገኙበታል።

በምረቃ መርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፤ ፖሊስ ሠራዊት ሕግ እንዲከበርና ሕዝቡ በሰላም ወጥቶ እንዲገባ ትልቅ ኀላፊነት አለበት።

ተመራቂዎችም በዩኒቨርሲቲው ያገኙትን ዕውቀትና ያላቸውን ልምድ በመጠቀም ሕዝብን ያለ ልዩነት፣ እና በእኩልነት ማገልግል እንዳለባቸው ምልዕክት አስተላልፈዋል።

ችግር ፈቺ የኾኑ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን ይበልጥ በማጠናከርና ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የወንጀል መከላከልና ምርመራ ሥራዎችን በማከናወን የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት ሊወጡ እንደሚገባም ተናግረዋል።

ዩኒቨርሲቲው የሀገሪቱን የፖሊስ ሠራዊት አቅም በትምህርትና ሥልጠና በመገንባት ረገድ ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው ጠቁመዋል። በየጊዜው የሥልጠና አድማሱን በማስፋት ለሠራዊቱ ተደራሽ ለማድረግ መሥራት እንዳለበትም ተናግረዋል፡፡

በአፍሪካ ተወዳዳሪ የምርምርና የፖሊስ ትምህርት ተቋም ኾኖ ለመገኘት የበለጠ መሥራት እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ለጎረቤት ሀገራት የፖሊስ ሠራዊትና መኮንኖች የሚሰጠው የትምህርት ዕድል የሚያኮራ ነው ብለዋል፡፡

ይህም ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር የሚኖራት ትስስር እንዲጠናከር ብሎም ሽብርተኝነትና ድንበር ተሸጋሪ ወንጀሎችን በጋራ ለመከላከል እየተደረገ ላለው ትብብርና ቅንጅት መጠናከር ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታልም ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ምክትል ኮሚሽነር ጄኔራል መስፍን አበበ፤ ዩኒቨርሲቲው የፌደራል ፖሊስና የክልል ፖሊስ ተቋማት፣ መንግሥትና ሕዝብ የጣለባቸውን አደራ በብቃት ለመወጣት እንዲችሉ ዘመኑ የሚፈልገውን የፖሊስ ክህሎትና ዕውቀት እያስጨበጠ ይገኛል፡፡

በዚህም ለሕገ-መንግሥቱ መከበር በፅናት የሚታገልና ዲሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብት አክብሮ የሚያስከብር ከዘመኑ ጋር አብሮ የዘመነ የፖሊስ አባላትን፣ መሪዎችን የማፍራት ተልዕኮውን በብቃት እየተወጣ መኾኑን ተናግረዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው በተለያዩ የፖሊስ የሙያ መስኮች ከአጫጭር ኮርሶች ጀምሮ እስከ ሁለተኛ ዲግሪ በማስተማር ለኢትዮጵያና ለምሥራቅ አፍሪካ ብቁ የኾኑ የፖሊስ መኮንኖችን እና ባለሙያዎችን በማፍራት ላይ መኾኑንም ጠቁመዋል፡፡

በምረቃ መርሐ-ግብሩ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴን ጨምሮ፣ የዩኒቨርሲቲው የቦርድ ሰብሳቢና የሥራ እና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል፣ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፈንታ፣ ከፍተኛ የፖሊስ መኮንኖችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች መታደማቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የለጎ ሐይቅ ፕሮጀክትን ተመለከቱ።
Next article“በርካታ ኀይልን ፈጻሚ ማድረግ የመሪነት ሚና ቢኾንም ውጤታማ መኾን የሚቻለው በትብብር ነው” ከንቲባ አዳነች አቤቤ