አካባቢን ጽዱ እና ውብ ለማድረግ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብ ሊያደርግ እንደሚገባ የምዕራብ ጎንደር ዞን አስታወቀ።

22

ገንዳ ውኃ: ሰኔ 22/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የምዕራብ ጎንደር ዞን ጤና መምሪያ “ጽዱ አካባቢ እና ጽዱ ጤና ተቋማት ለተሻለ ጤንነት” በሚል መሪ ሃሳብ ከባለድር አካላት ጋር በገንዳ ውኃ ከተማ የንቅናቄ መድረክ አካሂዷል።

ደረጃቸውን የጠበቁ የመጸዳጃ ቤቶችን ከመገንባት የተገነቡትንም በጥራት ከመያዝ እና በአግባቡ ከመጠቀም አኳያ ሰፊ ክፍተቶች እንዳሉ የዞኑ ጤና መምሪያ ምክትል ኀላፊ ዮወሴፍ ጉርባ ተናግረዋል።

የሕዝብ መጸዳጃ ቤቶች እና በመንግሥት አገልግሎት ሰጭ ተቋማት የሚገኙ መጸዳጃ ቤቶች ከፍተኛ የኾነ የጽዳት ችግር እንደሚታይባቸው ነው የተጠቀሰው።

በተለይም በመንግሥት ጤና ጣቢያ እና ሆስፒታሎች የሚገኙ መጸዳጃ ቤቶች በአግባቡ ባለመያዛቸው እና በየጊዜው ባለመጽዳታቸው ለተገልጋዮች ተጨማሪ የጤና ችግር እየፈጠረ መኾኑን ነው ያነሱት።

የግል እና የአካባቢ ንጽህናን ባለመጠበቅ ኅብረተሰቡ ለተለያዩ የጤና ችግሮች እየተጋለጠ በመኾኑ ደረጃቸውን የጠበቁ መጸዳጃ ቤቶች በመገንባት የግልን ብሎም የአካባቢን ንጽህና መጠበቅ ተቀዳሚ ተግባር ሊኾን እንደሚገባም ምክትል ኀላፊው አሳስበዋል።

አካባቢን ጽዱ እና ውብ ከማድረግ ባሻገር ጤናማ ማኅበረሰብ ለመፍጠር ሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብ ሊያደርግ ይገባልም ብለዋል።

የምዕራብ ጎንደር ዞን ተወካይ አሥተዳዳሪ ካሳሁን ከበደ አሁን ላይ ወቅቱ ክረምት እንደመኾኑ መጠን የኅብረተሰቡን ጤና አደጋ ሊጥሉ የሚችሉ ደረቅ እና ፈሳሽ ቆሻሻዎችን በአግባቡ ማስወገድ እንደሚገባም ተናግረዋል።

የቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓትን በማዘመን ጽዱ እና ውብ አካባቢን መፍጠር ይገባል ነው ያሉት ተወካይ አሥተዳዳሪዉ።

ቆሻሻን ሊጠየፍ የሚችል ማኅበረሰብ ለመፍጠር እና ተቋማትን ጽዱ ለማድረግ ባለድርሻ አካላት በትምህርት ቤቶች እና በጤና ተቋማት የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት መስጠት አለብን ብለዋል።

የዞኑ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ተወካይ ኀላፊ አግኝቼ አያሌው በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አነሳሽነት የተጀመረው ጽዱ ኢትዮጵያን የመገንባት ንቅናቄን ተግባራዊ ለማድረግ ሁሉም በእኔ ባይነት ስሜት ርብርብ ሊያደርጉ ይገባል ብለዋል። ጽዱ ተቋም ለመፍጠር ኅብረተሰቡ፣ የጤና ተቋማት፣ መሪዎች እና ባለሙያው በቅንጅት መሥራት አለበት ብለዋል።

የመድረኩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ኅብረተሰቡ ደረቅ እና ፈሳሽ ቆሻሻን ከማስወገድ ባሻገር መጸዳጃ ቤቶችን ገንብቶ በአግባቡ ከመጠቀም እና በጥንቃቄ ከመያዝ አኳያ የግንዛቤ ክፍተቶች እንዳሉ ተናግረዋል።

በመኾኑም የአካባቢን ጽዳት እና ውበት በዘላቂነት ለመጠበቅ የኅብረተሰቡን ግንዛቤ ማሳደግ ተቀዳሚ ተግባር መኾኑን አንስተዋል።

ተገቢውን የማኅበረሰብ ጤና አገልግሎት ለመስጠት በጤና ተቋማት የበጀት እጥረት ማነቆ መኾኑም በተሳታፊዎች ተነስቷል። በመኾኑም ተቋማት ግንዛቤ በመፍጠር እና በጀት በመመደብ በአካባቢ ንጽህና አጠባበቅ ሞዴል በመኾን ሊሠሩ ይገባል ተብሏል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በደሴ ከተማ ቆይታችን በሁሉም ቦታ እጅግ አመርቂ የኾኑ ሥራዎች እየተሠሩ መኾናቸውን አረጋግጠናል” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)
Next articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በደቡብ ወሎ ዞን ሐይቅ ከተማ የዘንድሮን የአረንጓዴ አሻራ አስጀመሩ።