ተመራቂ ተማሪዎች ሥራ ፈላጊ ሳይኾኑ ሥራ ፈጣሪ እንዲኾኑ በትኩረት መሠራቱን የሁመራ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ አስታወቀ።

24

ሁመራ፡ ሰኔ 22/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን የሁመራ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ በደረጃ አራት ያሠለጠናቸውን 80 ተማሪዎች አስመርቋል።

ተማሪዎቹ በአካውንቲግ፣ በአውቶሞቲቨ፣ በማኑፋክቸሪንግ እና በቢውልዲንግ ኤሌክትሪካል ኢንስታሌሽን ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የቆዩ ናቸው ።

የሁመራ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ዲን ጠጁ መሰለ ኮሌጁ የሰው ኀይል እና የግብዓት እጥረት እንዳለበት አንስተዋል።

ችግሩን በመቋቋም ከጉድለቶች ይልቅ ባሉ ነገሮች ላይ ትኩረት በማድረግ ተማሪዎችን በቁርጠኝነት በማስተማር ማስመረቅ ችለናል ብለዋል።

ተማሪዎች ተግባር ተኮር ትምህርትን እንዲወስዱ እና በመመዘኛ ፈተና ውጤታማ እንዲኾኑ ማድረግ ተችሏል ነው ያሉት።

ኮሌጁ ተማሪዎች ሥራ ጠባቂ ሳይኾን ሥራ ፈጣሪ እንዲኾኑ በትኩረት መሥራቱን የኮሌጁ ዲን ጠጁ አንስተው የማኅበረሰቡን ችግር የሚፈታ የደሮ መኖ ማቀነባበሪያ፣ የከብት መኖ እና የቡልኬት ማምረቻ ማሽኖችን መሥራት እንደተቻለም ገልጸዋል።

ተመራቂዎች በትምህርት ቆይታችሁ ያገኛችሁትን ዕውቀት በመጠቀም ማኅበረሰቡን በቅንነት እና በታማኝነት ልታገለግሉ ይገባል ያሉት ደግሞ የሁመራ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ዓለሙ አየነው ናቸው።

የወልቃይት ጠገዴ አማራ ሕዝብ ለዓመታት የማንነት ጥያቄ በማንሳቱ ግፍ ሲፈጸምበት የቆየ መኾኑን ተመራቂዎች የሚያውቁ በመኾናቸው ከምርቃት በኃላ የማኅበረሰቡ የማንነት ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ ሙያዊ እገዛ እና ድጋፍ እንዲያደርጉም መልዕክት አስተላልፈዋል።

ተመራቂ ተማሪዎች በበኩላቸው ኮሌጁ ለዓመታት ለሰጣቸው ዕውቀት እና ክብር ምሥጋና አቅርበው በተመረቁበት የሙያ መስክ ሥራ ፈጣሪ በመኾን ኅብረተሰባቸውን በቅንነት ለማገልገል እንደሚተጉም ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል።

ዘጋቢ፦ ያየህ ፈንቴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ኢትዮጵያ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲን ተግባራዊ በማድረግ ካጋጠማት የግጭት አዙሪት መውጣት አለባት” ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ.ር)
Next article“በደሴ ከተማ ቆይታችን በሁሉም ቦታ እጅግ አመርቂ የኾኑ ሥራዎች እየተሠሩ መኾናቸውን አረጋግጠናል” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)