“ኢትዮጵያ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲን ተግባራዊ በማድረግ ካጋጠማት የግጭት አዙሪት መውጣት አለባት” ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ.ር)

14

ባሕር ዳር፡ ሰኔ 22/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ እና በፌደራል አሥተዳደራዊ ሥነ ሥርአት አዋጅ ላይ ውይይት አድርገዋል::

በውይይቱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ.ር) በኢትዮጵያ የሽግግር ፍትሕን ተግባራዊ በማድረግ ባለፉት ጊዜያት ለተፈጸሙ በደሎች እና የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ተገቢውን ምላሽ መስጠት እንደሚገባት ተናግረዋል።

ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ.ር) ሀገራዊ ምክክር እና የሽግግር ፍትሕ ተመጋጋቢ እንደኾኑ እና ኢትዮጵያን ካለችበት ችግር ለማውጣት እንደሚያስችሉ ተናግረዋል።

የተለያዩ የዓለም ሀገራት የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲን ተግባራዊ በማድረግ ከፀረ ዲሞክራሲ ወደ ዲሞክራሲ ሥርአት፣ ከእርስ በርስ ግጭት ወደ ተረጋጋ ሀገረ መንግሥት ምስርታ እንደተሽጋገሩም አስረድተዋል።

በመኾኑም ኢትዮጵያ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲን ተግባራዊ በማድረግ ካጋጠማት የግጭት መውጣት እንዳለባት አስገንዝበዋል።

በዚህም የሕግ ተጠያቂነትን ማስፈን፣ እውነትን ማረጋገጥ፣ የተጎዱትን መጠገን ወይም የማካካሻ ሥርዓት ማበጀት እና ተገቢውን ክብር መስጠት፣ ተመሳሳይ በደሎች እንዳይከሰቱ መከላከል እና ብሔራዊ መግባባቶችን ማሳለጥ በዚሁ ማዕቀፍ የሚታይ መኾኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም ለፖሊሲው ውጤታማነት የምክር ቤቱ አባላት እና ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleከአማራ ክልል የሰላም ካውንስል የተሰጠ መግለጫ
Next articleተመራቂ ተማሪዎች ሥራ ፈላጊ ሳይኾኑ ሥራ ፈጣሪ እንዲኾኑ በትኩረት መሠራቱን የሁመራ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ አስታወቀ።