
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 15/2012 ዓ.ም (አብመድ) ሁሉንም የመከላከያ መንገዶች በመተግበር ሕዝቡ እራሱን ከቫይረሱ እንዲከላከል የአማራ ሀኪሞች ማኅበር ጥሪ አቀረበ፡፡
ወቅታዊውን ዓለም አቀፍ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በተመለከተ ከአማራ ሀኪሞች ማኅበር የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ
በወርሃ ታህሳስ መነሻውን ከቻይና ከውሀን ከተማ ያደረገው የኮሮና ቫይረስ ዓለምን ትልቅ ፈተና ውስጥ ከቷታል፡፡ ስርጭቱም ከቀን ወደ ቀን በመጨመር ለብዙ ዜጎች ስቃይና ሞት ምክንያት ሆኗል፡፡ በኢትዮጵያ እስካሁን 12 ሰዎች የኮሮና ቫይረስ እንደተገኘባቸው የኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትና የጤና ሚኒስቴር አስታውቀዋል፡፡ የአማራ ሀኪሞች ማኅበርም በሽታው ከተከሰተበት ቀን ጀምሮ ጉዳዩን በቅርበት ሲከታተልና ሙያዊ መረጃን ለሕዝብ በማድረስ የበኩሉን አስተዋፅኦ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡
አሁን የችግሩን አሳሳቢነት ለመረዳት የሚከተለውን የአቋም መግለጫ አውጥተናል፡፡
1. መንግስት ለጉዳዩ የሰጠውን ትኩረትና እያደረገ ያለው ጥረት የሚበረታታ ቢሆንም ቫይረሱ ካለው በከፍተኛ ፍጥነት የመስፋፋት ፀባይ (ካለን ዝቅተኛ የህክምና ባለሙያ ቁጥር፣ ውስን የጤና ተቋማት፣ ዝቅተኛ የግብዓት አቅርቦት አንፃር ከቁጥጥራችን ውጭ ሊሆን ስለሚችል በበላይ አካላት በሚሰጡት መመሪያዎችና መግለጫዎች ልክ እና ፍጥነት ተግባራዊ መሆናቸውን ማረጋገጥና ከፍተኛ ቁጥጥር እንዲደረግና የተጀመረው ጥረትም እንዲቀጥል እንጠይቃለን፡፡
2. በሽታው አዲስ እንደመሆኑ መጠን ከሙከራ ያለፈ የተረጋገጠ መድሀኒት የለውም፡፡ ስለዚህ ዋናው መፍትሄ መከላከልና መከላከል ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ ማኅበረሰቡ ከሚለቀቁ አሳሳች መረጃዎች እራሳችንን እንድንጠብቅና መረጃዎችንም ከታማኝ ምንጮች ብቻ ማለትም ከጤና ሚኒስቴር፣ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፣ ከጤና ቢሮዎች፣ ከሙያ ማኅበራትና ባለሙያዎች በመጠቀም የራሳችንን ንፅህና በመጠበቅ፣ ባለመሰባሰብ ከሚስሉ ሰዎች ራሳችንን በማራቅ፣ እጃችንን ሳንታጠብ አይንና አፍንጫችንን ባለመንካት አስፈላጊና የግድ ካልሆነ በቀር ከቤት ባለመውጣትና መረጃዎችን ለሌሎቹ በማካፈል እራሳችን ከበሽታ እንድንከላከል እናሳስባለን፡፡
3. የበሽታው ምልክቶች ከተለያዩ በሽታዎች ጋር ተቀራራቢ ስለሆኑ በሽታው በትክክል የሚረጋገጠው በምርመራ ብቻ በመሆኑ መንግስት የመመርመሪያ መሳሪያና ኪቶችን በተቻለ መጠን ተተደራሽ እንዲያደርግ፤ ማኅበረሰቡም ምልክቶቹ ማለትም፡- ደረቅ ሳል፣ ከፍተኛ የሆነ የሰውነት ሙቀት፣ ትንፋሽ ማጠር ካሉ ቶሎ ወደ ጤና ተቋማት በመሄድ እራስን በመለየት፣ በመመርመር የራሳችንንም ሆነ የወገኖቻችን ህይወት እንድንታደግ እናሳስባለን፡፡
4. የሚዲያ ተቋማትና የማኅበራዊ ሚዲያ አንቂዎች ለጉዳዩ የሰጣችሁት ትኩረትና የማኅበረሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ እያደረጋችሁት ያለውን ጥረት እያደነቅን መልዕክቶታችሁ ልዩ ፍላጎት ያላቸውን ማለትም ዐይነ ሥውራንንና መስማት የተሳናቸውን፣ የአእምሮ ውስንነት ያለባቸውን ያገናዘበ እንዲሆን፣ የምታስተላልፏቸው መልዕክቶች ሰፊ ተደራሽነት ያላቸው በመሆኑ መልዕክቶቹ የባለሙያ ምክረ ሀሳብ ያላቸው እንዲሆኑና ስህተቶች ሲኖሩ ቶሎ ማስተካከያ እንድትሰጡ፤ አሁንም ትኩረታችሁን አጠናክራችሁ እንድትቀጥሉ እናሳስባለን፡፡
5. ለሲቪክና በጎ አድራጎት ማኅበራት፣ ለወጣት ማኅበራት ለፖለቲካ ድርጅቶች አሁን የገጠመን ችግር በጤና ባለሙያዎችና በመንግስት ብቻ የሚፈታ ባለመሆኑ ሁላችሁም ያላችሁን አደረጃጀት በመጠቀም ማኅበረሰብ በማስተማር፣ ግብዓቶችን በማቅረብና በሽታውን በመከላከል የተቋቋሙ ግብረ ሀይሎች የሚሰጡትን መመሪያዎች ተፈፃሚ እንዲሆኑ የበኩላችሁን አስተዋፅኦ እንድታደርጉ ጥሪ እናቀርባለን፡፡
6. ለጤና ባለሙያዎች ይህ በሽታ ከተከሰተ ጊዜ አንስቶ የበሽታውን አሳሳቢነት በመረዳት ግንዛቤ በመፍጠር የሚመለከታቸውን አካላት ግፊት በማድረግ ከምንም በላይ እንደተለመደው ለሕዝባችን እራሳችሁን አሳልፋችሁ ለመስጠት ያላችሁን ዝግጁነት በማየት ከፍተኛ የሆነ ምስጋና እናቀርባለን፡፡ አሁንም ቢሆን ችግሩን ከባለሙያ በላይ የሚረዳው የለምና በየተቋማችሁ ግንባር ቀደም በመሆን ለተጠራው ብሔራዊ ግዳጅ እራሳችሁን በሙያም ሆነ በሞራል ከመቼውም ጊዜ በላይ ዝግጁ እንድታደርጉ እያሳሰብን መንግስትም ወታደር ያለ ትጥቅ እና ስንቅ አይወጣምና አስፈላጊውን ግብዓትና እራስን የመከላከያ መንገዶች በሚቻለው ሀቅም ሁሉ እንዲዘጋጁ ጥሪያችን እናስተላልፋለን፡፡
7. በውጭ የምትኖሩ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን በተለይም የህክምና ባለሙያዎች የኮሮና ቫይረስ ሃያላን ሀገራትን ሁሉ በእጅጉ የፈተነ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ስለዚህ ይህንን ወረርሽኝ ለመቆጣጠር መንግስት እና ሕዝብ በሚያደርጉት ትግል ከምንጊዜውም በላይ ከጎናችን በመቆም የምትችሉትን ሁሉ እንድታደርጉ ጥሪ እናስተላልፋለን፡፡
8. ማኅበራችን የአማራ ሀኪሞች ማኅበር አብዛኛው ተግባራትን በማቆም ሙሉ ትኩረቱን ወደዚህ ወረርሽኝ አድርጓል፡፡ በዚህም መጋቢት 26 እና 27/2012 ዓ.ም ሊካሄድ የነበረውን የአማራ የጤና ጉባኤ (Amhara health Fair) ላልተወሰነ ጊዜ አራዝሟል፡፡ የማኅበሩን አደረጃጀቶችና የመገናኛ አውታሮችን በመጠቀም ስለ በሽታው ወቅታዊ መረጃና ግንዛቤ ስናደርስ ቆይተናል፡፡ ወደፊትም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር ማኅብረሰቡን የማስተማር፣ በዚህ ሥራ ላይ ለሚሰማሩ ባለሙያዎችና በጎ አድራጊዎች ስልጠናዎችን በመስጠት ሙያዊ ግዴታችን ከመቼውም ጊዜ በላይ በመወጣት በሽታውን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር በሚደረጉ ጥረቶች ሁሉ የምንችለውን ሁሉ ለማድረግ ያለንን ቁርጠኝነት በመግለፅ አብሮ መስራት ለሚፈልጉ አካላት በዚህ አጋጣሚ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡
የአማራ ሀኪሞች ማኅበር
መጋቢት 15/2012 ዓ.ም
ባሕር ዳር