በደቡብ ጎንደር ዞን ክትባት ያልወሰዱ ሕጻናትን የመለየት ሥራ እየተሠራ መኾኑን ዞኑ አስታወቀ፡፡

15

ባሕር ዳር፡ ሰኔ 22/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ሕጻናትን ከተለያዩ ወረርሽኞች ለመጠበቅ እና ክትባት ለመስጠት የመለየት ሥራ በሁሉም ወረዳዎቹ እየሠራ መኾኑን የደቡብ ጎንደር ዞን ጤና መምሪያ አስታውቋል፡፡

በደቡብ ጎንደር ዞን ሕጻናት በኮረና ቫይረስ ወረርሽኝ እና ከዛም በኋላ በተለያዩ ምክንያቶች ክትባት ያልወሰዱ ሕጻናትን በመለየት ክትባቱን ለመስጠት የቤት ለቤት የቆጠራ እና ልየታ ሥራ እየተሠራ ስለመኾኑ ነው የተገለጸው፡፡

የዞኑ ጤና መምሪያ ኀላፊ ሙላት አሸናፊ ለአሚኮ እንዳሉት በዞኑ ባለፉት ጊዜያት በተካሄደው የክትባት ዘመቻ 82 በመቶ በዞኑ የሚገኙ ሕጻናትን በክትባቱ ተደራሽ ማድረግ ተችሏል፡፡

ክትባቱ ሕጻናትን ከተለያዩ ወቅታዊ ወረርሽኞች ለመከላከል ታሳቢ ያደረገ ስለመኾኑም ነው የነገሩን፡፡ በክትባቱ እንደ ኩፍኝ፣ ትክትክ፣ ኒሞኒያ እና ከመሰል በሽታዎች ሕጻናትን መጠበቅ እንደሚያስችል አስገንዝበዋል፡፡

በቆጠራው አልተከተቡም ተብለው ከተያዙ 18 በመቶ ሕጻናት ቁጥሩ ከፍም ዝቅም ሊል ስለሚችል ቆጠራው ቤት ለቤት በጥንቃቄ እንዲካሄድ እየተደረገ ስለመኾኑም ነው ያስገነዘቡት፡፡

ሕጻናትን ከተለያዩ ወረርሽኞች ለመጠበቅ ባለ 15 ጸረተሕዋስያን ክትባትን መውሰድ ይኖርባቸዋል ያሉት ኀላፊው በዚህ ሂደት ሁሉም ሕጻናት መውሰድ ሚገባቸውን ክትባቶች መውሰድ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡

አንድ ሕጻን አንደኛውን ክትባት ወስዶ ሌላኛውን ክትባት ሳይወሰድ ሊቀር ስለሚችል ይህ እንዳይኾን ትኩረት ሰጥቶ የመለየት ሥራ እየተሠራ ስለመኾኑ ነው ያብራሩት፡፡

አቶ ሙላት ኅብረተሰቡ ክትባቱ ያለውን ጠቀሜታ በመገንዘብ ትክክለኛ መረጃ በመስጠት 5 ዓመት እና በታች ያሉ ሙሉ ክትባትን ያልወሰዱ ሕጻናትን በተመለከተ ክትባቱን እንዲወስዱ ለማድረግ መረጃ እንዲሰጡ ጠይቀዋል፡፡

ኀላፊው ክረምቱን ተከትሎ ሊከሰት የሚችልን ወረርሽኝ ቀድሞ ለመከላከል ዞኑ በ14 ወረዳዎች ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ እንደሚገኝም አስገንዝበዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎቹን እያስመረቀ ነው፡፡
Next article“የሕጻናት ህመም እና ሞትን ለመቀነስ በሥርዓተ ምግብ ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ይገባል” የሰሜን ወሎ ዞን ጤና መምሪያ