
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 22/2016 ዓ.ም (አሚኮ) «የፊስካል ፌዴራሊዝም መሠረታዊ ጉዳዮች እና የኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ» በሚል መሪ መልዕክት ለፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት ሥልጠና እየተሠጠ ነው፡፡
በዚህ መድረክ ላይ የተገኙት የኢፌዴሪ ፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ፍትሐዊ የሃብት ክፍፍል፣ ውጤታማ የፊስካል ሽግግር እና በክልሎች መካከል የተመጣጠነ ዕድገትን ማረጋገጥ ለጠንካራ የፌዴራል ሥርዓት ጽኑ መሠረቶች መኾናቸውን ገልጸዋል፡፡
ፌዴራላዊ ሥርዓት ከሌሎች ሥርዓተ መንግሥታት በተሻለ ደረጃ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ፣ የሕዝቦችን በእኩልነት አብሮ የመኖር እና በጋራ የመበልፀግ ዓላማ ለማሳካት የሚያስችል ሥርዓት እንደኾነም አስታውሰዋል፡፡
ለሥርዓቱ ዘላቂነት ፍትሐዊ የሃብት ክፍፍል፣ ውጤታማ የፊስካል ሽግግር እና በክልሎች መካከል የተመጣጠነ ዕድገትን ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል፡፡
አፈ ጉባኤ አገኘው ያልተማከለ የፋይናንስ አሥተዳደር በሚከተሉ ሀገራት ተግባራዊ ከሚደረጉ የፊስካል ሽግግሮች አንዱ የጋራ ገቢ ክፍፍል እንደኾነ አስገንዝበዋል፡፡
በአንዳንድ ሀገራት የፊስካል ሽግግር የፌዴራል መንግሥት እና የበታች የአሥተዳደር አካላት የጋራ ተብለው ከተለዩ የገቢ ዓይነቶች ላይ የገቢ ወይም የታክስ ምጣኔን በመጋራት የገቢ ክፍፍል የሚያደርጉ ሲኾን በሌሎች ሀገራት ደግሞ የጋራ ተብለው በተለዩ ገቢዎች ላይ ታክስ የመጣል እና የመሠብሠብ ሥልጣን ለፌዴራል መንግሥት ብቻ በመስጠት የፌዴራል መንግሥቱ የሠበሠበውን ገቢ በተለያየ መርህ ላይ በመመሥረት ገቢው በፌዴራል መንግሥት እና በክልሎች መካከል እንደሚከፋፈል አስረድተዋል፡፡
አፈ ጉባኤው በክልሎች መካከል የተመጣጠነ ዕድገትን ለማረጋገጥ እና ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን የሚዘጋጁ ቀመሮችን፣ ምክረ ሃሳቦችን፣ የሕግ ማዕቀፎችን እና የአሠራር ሥርዓቶችን ጥራት በማረጋገጥ እንዲሁም ተግባራዊ እንዲኾኑ በማድረግ ረገድ ምክር ቤቱ የማይተካ ሚና እንዳለው ተናግረዋል፡፡
የምክር ቤቱ አባላት በዕውቀት እና በመረጃ ላይ የተመሠረተ ውሳኔ ለማሳለፍ እንዲህ አይነቱ ሥልጠና ያለው ጠቀሜታ በእጅጉ የጎላ እንደኾነ አመላክተዋል፡፡
የኢፌዴሪ ፌዴሬሽን ምክር ቤት በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት እና የምክር ቤቱን ሥልጣን እና ተግባር ለመዘርዘር ተሻሽሎ በወጣው አዋጅ መሠረት የክልሎች እና የፌዴራሉ መንግሥት የጋራ ተብለው የተመደቡ ገቢዎች በሁለቱ መካከል የሚከፋፈልበትን እንዲሁም የፌዴራሉ መንግሥት ለክልሎች ድጎማ የሚሰጥበትን ቀመር እንደሚወስን በግልጽ ተደንግጓል፡፡
ዘጋቢ፦ በለጠ ታረቀኝ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!