የአጓት ውኃ የአፈር ግድብ መጠናቀቅ የአካባቢው አርሶ አደሮች በዓመት ከሁለት ጊዜ በላይ እንዲያመርቱ እድል የሚሰጥ መኾኑ ተገለጸ።

12

ባሕር ዳር: ሰኔ 21/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአጓት ውኃ የአፈር ግድብ በደቡብ ጎንድር ዞን በስማዳ ወረዳ በ182 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር ወጭ የተገነባ ፕሮጀክት ነው።

የግድቡ ግንባታ እንደተጠናቀቀ እና በቅርቡ እንደሚመረቅ የተናገሩት የደቡብ ጎንድር ዞን መስኖ እና ቆላማ አካባቢዎች ልማት መምሪያ ተወካይ ኅላፊ አድጎ ለአከባቢው አርሶ አደሮች ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው የጎላ መኾኑን አስረድተዋል።

ተወካይ ኅላፊው አድጎ ጫኔ የግድቡ ግንባታ የተጀመረው በ2009 ዓ.ም ቢኾንም እስካሁን ድረስ ከፍተኛ የመልካም አሥተዳደር ችግር ኾኖ እንደቆየ አስታውሰዋል፡፡

ተወካይ ኅላፊው እንደገለጹት ግድቡ ሥራ ሲጀምር ከዓመት አንድ ጊዜ ብቻ ያመርቱ የነበሩት የአካባቢው አርሶ አደሮች በዓመት ሁለት ጊዜ እና ከዛ በላይ እንዲያመርቱ እድል ይሰጣል ነው ያሉት፡፡

የግድቡ መጠናቀቅን ተከትሎ በዘንድሮው የምርት ዘመን አርሶ አደሮች መስኖን በመጠቀም በቆሎ፣ ስንዴ፣ ሽንኩርት፣ ድንች፣ ጥቅል ጎመን፣ ሰላጣ፣ ገብስ እና የመሳሰሉትን ሰብሎች እንዲያመርቱ አስችሏል ነው ያሉት።

አርሶ ደሮቹ ከምግብ ፍጆታ ባለፈ ምርታቸውን ለገበያ በማዋል ተጨማሪ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንዲያገኙ የሚያስችል መኾኑን ነው ኅላፊው የገለጹት፡፡

የግድቡ የግንባታ ሥራ በውኃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን (ውሥኮድ) የተከናወነ ሲኾን የማማከር ሥራው ደግሞ በልህቀት ጥናት እና ዲዛይን ቁጥጥር ኮርፖሬሽን የተከናወነ እንደኾነ ተገልጿል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ቀድሞ ከሚታወቅባቸው አገልግሎቶቹ ልቆ ለመምጣት ከፍተኛ ጥረት ላይ እንደሚገኝ ገለጸ።
Next article“ፍትሐዊ የሃብት ክፍፍል እና በክልሎች መካከል የተመጣጠነ ዕድገትን ማረጋገጥ ለጠንካራ የፌዴራል ሥርዓት ጽኑ መሠረቶች ናቸው” አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር