ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ቀድሞ ከሚታወቅባቸው አገልግሎቶቹ ልቆ ለመምጣት ከፍተኛ ጥረት ላይ እንደሚገኝ ገለጸ።

19

ደሴ: ሰኔ 21/2016 ዓ.ም (አሚኮ) “በአዲስ መንፈስ ለላቀ ከፍታ” በሚል መሪ ሀሳብ ወደ ሥራ የገባው የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ከሚታወቅባቸው አገልግሎቶቹ ልቆ ለመምጣት በከፍተኛ ጥረት ላይ እንደሚገኝ የባንኩ ሥራ አስፈጻሚ እመቤት መለሰ (ዶ.ር) ተናግረዋል።

የባንኩ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በደሴና ኮምቦልቻ ከተማ ከሚገኙ ደንበኞች እና ከባንኩ ባለድርሻ አካላት ጋር ተወያይተዋል። ከነበረበት ችግር በመውጣት ለደንበኞች የተሻለ አገልግሎት መስጠት መጀመሩንም ባንኩ ገልጿል።

የባንኩ ሥራ አስፈጻሚ እመቤት መለሰ ( ዶ.ር) እንዳሉት ባለፉት አራት ወራት ባንኩ ካጋጠሙት ችግሮች ለመውጣት የሠራ ሲኾን በዚህ ወቅትም በሚታወቅባቸው አገልግሎቶች ደንበኞቹ ጋር እየደረሰ መኾኑን ተናግረዋል።

ከዚህ በፊት በጊዜያዊነት ተቋርጠው የነበሩ ክፍያዎች እየተከፈሉ ሲኾን የብድር አገልግሎትም በቅርቡ እንደሚጀምር ተጠቁሟል።

ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ቀድሞ ከሚታወቅባቸው አገልግሎቶቹ ልቆ ለመምጣት በከፍተኛ ጥረት ላይ እንደሚገኝም ሥራ አስፈጻሚዋ ተናግረዋል።

በደሴ ከተማ እና አካባቢው እንዲሁም በሌሎች ከተሞችም ተደራሽነቱን ለማስፋት የታቀደ ሲኾን ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት የሚሰጥባቸውን ቅርንጫፎች ወደ ሥራ ለማስገባት እና የዲጂታል ባንኪንግ አገልግሎቱ የተሳለጠ እንዲኾን እየተሠራ መኾኑም ተመላክቷል።

ደንበኞች ባንኩ በአዲስ መንፈስ እና በላቀ ከፍታ ወደ ሥራ የገባ መኾኑን ዐውቀው ለሀገር እድገት እና ከፍታ በጋራ እንዲሠሩ ጥሪ ቀርቧል።

ዘጋቢ፦ ጀማል ይማም

Previous article“ከነጻነት ማግስት በአማራ ምድር በጠገዴ ወረዳ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የቴክኒክና ሙያ ተማሪዎችን በማስመረቃችን እንኳን ደስ ያላችሁ” የጠገዴ ወረዳ አሥተዳዳሪ ጌታሁን ብርሃኔ
Next articleየአጓት ውኃ የአፈር ግድብ መጠናቀቅ የአካባቢው አርሶ አደሮች በዓመት ከሁለት ጊዜ በላይ እንዲያመርቱ እድል የሚሰጥ መኾኑ ተገለጸ።