
ሁመራ: ሰኔ 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን የጠገዴ ወረዳ ማክሰኞ ገበያ ቴክኒክ እና ሙያ ማሠልጠኛ ተቋም ለሦስት ዓመት ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የነበሩ 151 ተማሪዎችን አስመርቋል።
ተመራቂዎቹ በአካውንቲግ እና በአይሲቲ የትምህርት ዘርፍ ትምህርታቸውን ሲከታተሉ ቆይተዋል።
በወረዳው የቴክኒክ እና ሙያ ማሠልጠኛ ተቋም ባለመኖሩ ተማሪዎች ወደ ሌላ ቦታ በመሄድ ይማሩ እንደነበር የጠገዴ ወረዳ አሥተዳዳሪ ጌታሁን ብርሃኔ አስታውሰዋል።
በዚህም ተማሪዎች እና ወላጆች ለተለያየ የኢኮኖሚ ችግር ይጋለጡ እንደነበር ነው የተናገሩት።
ከዞኑ የነጻነት ማግስት የወረዳው መሪዎች እና ኅብረተሰቡ በአንድነት በመሥራቱ ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ የቴክኒክ እና ሙያ ሕንጻ ግብዓት በማሟላት የመማር ማስተማር ሂደት እንዲጀምር በመደረጉ ተማሪዎችን በወረዳው በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ አስመርቀናል ብለዋል።
ለተመራቂዎች እንኳን ደስ ያላችሁ ያሉት የወረዳ አሥተዳዳሪው በቀጣይ በተመረቃችሁበት የሙያ መስክ ሥራ ፈጣሪ ልትኾኑ ይገባል ነው ያሉት።
የጠገዴ ወረዳ ማክሰኞ ገበያ ቴክኒክ እና ሙያ ማሠልጠኛ ተቋም ዲን ሀጎስ መኮንን ማሠልጠኛ ተቋሙ የተለያየ የግብዓት አቅርቦት ችግር ቢኖርበትም ችግሩን በመቋቋም በርብርብ በመሠራቱ ተማሪዎችን ለምርቃት ማብቃት እንደተቻለ ተናግረዋል።
በወረዳው የተማረ የሰው ኀይል እንዳይኖር በባለፈው ሥርዓት የተለያየ ጫና የደረሰ ቢኾንም ከነጻነት ማግሥት በቁጭት እና በቁርጠኝነት በመሠራቱ ተማሪዎችን ለፍሬ ማብቃት ተችሏል ነው ያሉት።
ተቋሙ ተማሪዎችን ማስመረቅ በመቻሉ ኅብረተሰቡ ደስተኛ መኾኑን አንስተው በቀጣይም የተማረ የሰው ኀይል ለማፍራት በቁርጠኝነት እንደሚሠራም ተናግረዋል።
የወረዳው ቴክኒክ እና ሙያ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በማስመረቁ እና ተመራቂ ተማሪ በመኾናቸው ደስተኛ መኾናቸውን አስተያየታቸውን ለአሚኮ የሰጡ ተመራቂዎች አንስተዋል።
በቀጣይ በተመረቁበት የሙያ መስክ የመንግሥት ቅጥር ከመጠበቅ ይልቅ ሥራ ፈጣሪ በመኾን ማኅበረሰባቸውን በቅንነት ለማገልገል ቁርጠኛ መኾናቸውን ገልጸዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!