እየተስተዋለ ያለውን በትጥቅ የታገዘ የሰዎች እገታ ከምንጩ ለማድረቅ ሕዝቡ ተባባሪ መኾን እንዳለበት ተጠቆመ።

19

ጎንደር: ሰኔ 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በጎንደር ከተማ አስተዳደር እየተበራከተ የመጣውን በመሳሪያ የታገዘ የእገታ ወንጀል ለመከላከል ከምሽቱ 12: 00 ሰዓት ጀምሮ በባለ ሦስት እግር ተሽከርካሪዎች ላይ የእንቅስቃሴ ገደብ ተጥሏል።

የጎንደር ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ ኀላፊ ረዳት ኮሚሽነር አየልኝ ታክሎ በከተማዋ እየተበራከተ በመጣው የእገታ ወንጀል ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል።

የመምሪያው ኀላፊው በጎንደር ከተማ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሰው እገታ ወንጀል እየተበራከተ መምጣቱን አስታውቀዋል።

መምሪያ ኀላፊው በመግለጫቸው የታጠቁ ግለሰቦች በከተማዋ ነዋሪዎች ላይ የእገታ ወንጀል እየፈጸሙ መኾናቸውን አንስተው ታጋቾች ከፍተኛ ገንዘብ እንዲከፍሉ እየተገደዱ መኾኑን እና ለተለያዩ ሰብዓዊ ጉዳቶች እየተዳረጉ መኾኑንም አረጋግጠዋል።

ከተማ አስተዳደሩ የከተማዋ ነዋሪዎችን ደኅንነት ለማረጋገጥ በሠራው ሥራም ከእገታ ወንጀል ጋር በተያያዘ የተጠረጠሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ረዳት ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።

የተለያዩ ወንጀሎች በከተማዋ ሲፈጸሙ ተባባሪ ናቸው ተብለው የተጠረጠሩ 27 ባለ ሦስት እግር ተሽከርካሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ያነሱት ረዳት ኮሚሽነሩ ተሽከርካሪዎቹ ታርጋ የሌላቸው መኾኑንም ጠቁመዋል።

በቁጥጥር ስር ከዋሉት ባለ ሦስት እግር ተሽከርካሪዎች መካከል አራቱ በእገታ ወንጀል ተሰማርተዋል ተብለው የተጠረጠሩ ተሽከርካሪዎች መኾናቸውን አስታውቀዋል።

የከተማ ፈቃድ እና ታርጋ የሌላቸው ባለ ሦስት እግር ተሽከርካሪዎች በከተማዋ ተበራክተዋል ያሉት ኀላፊው ከዛሬ ሰኔ 15/2016 ዓ.ም ጀምሮ ከምሽቱ 12 ሰዓት በኋላ የባላ ሦስት እግር ተሽከርካሪ እንቅስቃሴ መታገዱን አስታውቀዋል። ከዚህ ሰዓት በኋላ የሚገኝ ባለ ሦስት እግር ተሽከርካሪ በሕግ ተጠያቂ ይኾናል ተብሏል። የእንቅስቃሴ ገደቡ ሕገ ወጥ ድርጊቱን መቆጣጠር እስኪቻል ድረስ ይቆያል ብለዋል።

እንደ መምሪያ ኀላፊው ረዳት ኮሚሽነር አየልኝ ታክሎ ገለጻ በከተማዋ እየተበራከተ የመጣውን የእገታ ወንጀል ለመከላከል የምርመራ ቡድን ተቋቁሞ እየተሠራ ነው።

የእገታ ወንጀል በጎንደር ከተማ በ2013 ዓ.ም ተከስቶ የነበር ሲኾን ማኅበረሰቡ ከጸጥታ ኃይሉ ጋር በመተባበር እና ተጠርጣሪዎችን በመጠቆም ባደረገው ጉልህ አስተዋጽኦ ወንጀሉን ማስቆም መቻሉን አስታውሰዋል።

ማኅበረሰቡ የተለመደ ትብብሩን በማድረግ የወንጀሉ ፈጻሚዎች ተጠያቂ እንዲኾኑ የበኩሉን እንዲወጣ መምሪያ ኀላፊው ረዳት ኮሚሽነር አየልኝ ታክሎ መልክት አስተላልፈዋል።

በምሽት የሚፈጸሙ ወንጀሎችን ለመከላከልም ማኅበረሰቡን ያሳተፈ የብሎክ አደረጃጀት በከተማ አስተዳደሩ ተግባራዊ እየተደረገ መኾኑ በመግለጫው ተመላክቷል።

ዘጋቢ:- ኃይሉ ማሞ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየጅጋ ከተማ ነዋሪዎች በአካባቢያቸው ሰላም ዙሪያ መከሩ።
Next articleበኮምቦልቻ ከተማ የተሻለ አፈጻጸም ለነበራቸው የፖሊሰ አባላት ዕውቅና እና ሽልማት ተበረከተላቸው፡፡