
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የምዕራብ ጎጃም ዞን ኮማንድ ፖስት ከጅጋ ከተማ አሥተዳደር ነዋሪዎች ጋር በአካባቢው ሰላም ዙሪያ መክሯል።
የምሥራቅ ዕዝ ኮር ምክትል አዛዥ ለኦፕሬሽናል ኮሎኔል ሰጥዬ አራጌ፣ የምዕራብ ጎጃም ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ እና የሰላምና ጸጥታ መምሪያ ኀላፊ አበባው አንተነህ እንዲሁም የምዕራብ ጎጃም ዞን የፖለቲካ እና የአቅም ግንባታ ዘርፍ ኀላፊ ሙላት ጌታቸው በምክክሩ ተገኝተዋል።
መሪዎቹ የሰላም ዋጋ ከፍ ያለ በመኾኑ ሁሉም ዜጋ ለሰላም ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንዳለበት ጠቁመዋል።
ባለፉት 10 ወራት ነፍጥ ያነሱ ቡድኖች የሕዝቡን ችግር እና ሰቆቃ ከማባባስ ውጭ ምንም ያመጡት መፍትሔ እንደሌለ ገልጸው መንግሥት የክልሉን፣ የዞኑን ብሎም የከተማውን ሰላም በዘላቂነት ለማረጋገጥ ቁርጠኛ ነው ብለዋል።
የምሥራቅ ዕዝ ኮር ምክትል አዛዥ ለኦፕሬሽናል ኮሎኔል ሰጥየ አራጌ መከላከያ ሠራዊቱ በየትኛውም የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚከሰቱ ችግሮችን ለመፍታት ተልዕኮ የተሰጠው በመኾኑ በምዕራብ ጎጃም ዞንም ግዳጁን በብቃት እና በጥንቃቄ እየፈፀመ እንደኾነ ተናግረዋል።
የሀገር መከላከያ ሠራዊት በማኅበራዊ ትስስር ገጹ እንዳለው የአካባቢው ሰላም እንዲመለስ የሃይማኖት መሪዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የመንግሥት ሠራተኞች፣ ወጣቶች እና ኅብረተሰቡ ሳይታክቱ ከመከላከያ እና ከክልሉ የጸጥታ ኀይል ጋር በመተባበር እንዲሠሩም አሳስበዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!