“ተሳትፏዊ ግብርና እና የአየር ንብረት ሽግግር” መርሐ ግብር ይፋ ተደረገ፡፡

19

ባሕር ዳር: ሰኔ 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ከ166 ሺህ በላይ የአርሶ አደር ቤተሰቦችን ከድኅነት በማላቀቅ ዘላቂ የምግብ ዋስትናቸውን ያረጋግጣል የተባለለት “ተሳትፏዊ ግብርና እና የአየር ንብረት ሽግግር” መርሐ ግብር ይፋ ተደርጓል፡፡

በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙትን የኅብረተሰብ ክፍሎች የምግብ ዋስትናቸውን እንዲያረጋግጡ የሚያስችል “ተሳትፏዊ ግብርና እና የአየር ንብረት ሽግግር” የማስጀመሪያ መርሐ ግብር ዛሬ በባሕር ዳር ከተማ ተካሂዷል።

በሥነ ሥርዓቱ ላይ በአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የተሳትፏዊ ግብርና እና የአየር ንብረት ሽግግር መርሐ ግብር ሥራ አሥኪያጅ በለጠ ጌታነህ እንዳሉት መርሐ ግብሩ ትኩረት የሚያደርገው የምግብ ዋስትናቸውን ባላረጋገጡ 10 ዞኖች፣ በ20 ወረዳዎች እና በ33 የተመረጡ አካባቢዎች ነው።

የመርሐ ግብሩ ዓላማ በተቀናጀ የግብርና ሥራ ማኅበረሰቡን አሳታፊ በማድረግ፣ ምርታማነትን ማሳደግ እና የአርሶ አደሩን ሕይዎት ማሻሻል እንደኾነ ገልጸዋል።

እቶ በለጠ አርሶ አደሮች የአየር ንብረት መዛባትን የሚጠብቁ የተለያዩ ተግባራትን በማከናዎን የመሬትን ምርታማነት የሚጨምሩ ሥራዎችም ይተገበራሉ ነው ያሉት።

አርሶ አደሩ ክረምትን ብቻ ጠብቆ ከማምረት ተላቅቆ ዓመቱን ሙሉ በመስኖ እንዲያለማ የመስኖ አውታሮች እና የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሥራዎችም እንደሚከናዎኑ አቶ በለጠ ጠቁመዋል። አርሶ አደሩን ከቴክኖሎጅ ጋር በማስተዋወቅም የተሻሻሉ አሠራሮችን እንዲላመድ ይደረጋል ብለዋል።

ሥራ አሥኪያጁ የፌዴራል መንግሥት በአማራ ክልል ለሚተገበረው “የተሳትፏዊ ግብርና እና የአየር ንብረት ሽግግር ” መርሐ ግብር ማስፈጸሚያ 37 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር መመደቡን ተናግረዋል።

የግብርና ቢሮ ምክትል ኀላፊ አጀበ ስንሻው በመርሐ ግብሩ የግብርናውን ሥራ ደጋፊ የኾኑ ሌሎች ተግባራትም ይከናወኑበታል ብለዋል።

ምክትል ቢሮ ኀላፊው በዚህ መርሐ ግብር ምርት እና ምርታማነትን የሚጨምሩ ሥራዎች ይሠሩበታል፤ የመስኖ አውታሮች ይገነቡበታል፤ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሥራም ይከናወንበታል ነው ያሉት።

በመርሐ ግብሩም ከ166 ሺህ በላይ የአርሶ አደር ቤተሰቦችን ከድኅነት በማላቀቅ ዘላቂ የምግብ ዋስትናቸውን እንዲያረጋግጡ ያስችላል ነው ያሉት።

በፌዴራል መንግሥት የ”ተሳትፏዊ ግብርና እና የአየር ንብረት ሽግግር “ዋና ሥራ አሥኪያጅ ኑረዲን አሣሮ እንዳሉት የአማራ ክልል ከ40 በመቶ በላይ የግብርናውን ድርሻ የያዘ በመኾኑ ይህን ክልል በማልማት የዜጎችን የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ ማለት የሌሎችንም ክልሎች ነዋሪዎች የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ ነው። ክልሉ ሲለማ ከራሱ ባለፈ ለሌሎችም ይተርፋል ነው ያሉት።

ዋና ሥራ አሥኪያጁ እንዳሉት በመርሐ ግብሩ አርሶ አደሮች ምርት እና ምርታማነትን እንዲያሳድጉ ሢሠራ ጎን ለጎንም የገበያ ትስስር ይፈጠርላቸዋል ብለዋል።

መርሐ ግብሩ ሴቶችን፣ አካል ጉዳተኞችን እና ወጣቶችን አሳታፊ እንደሚያደርግ አቶ ኑረዲን አሳሮ ጠቁመዋል።

ይህ “የተሳትፏዊ ግብርና እና የአየር ንብረት ሽግግር” በአማራ ክልል የሚተገበረው ለተከታታይ ሰባት ዓመታት እንደሚኾን ከግብርና ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያስረዳል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየጉበት በሽታ አንዱ የማኅበረሰብ ስጋት በመኾኑ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሠራ እንደሚገባ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አሳሰበ፡፡
Next articleየጅጋ ከተማ ነዋሪዎች በአካባቢያቸው ሰላም ዙሪያ መከሩ።