የጉበት በሽታ አንዱ የማኅበረሰብ ስጋት በመኾኑ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሠራ እንደሚገባ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አሳሰበ፡፡

20

ደሴ፡ ሰኔ 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ተቋሙ ስር የሰደደ የጉበት በሽታን በተመለከተ ከባለድርሻ አካላት ጋር በደሴ ከተማ የምክክር መድረክ አካሂዷል።

የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የተቋቋመበት አንዱ ዓላማ ጤና እና ጤናነክ በኾኑ ጉዳዮች ላይ ጥናት እና ምርምሮችን ማካሄድ ነው። ተቋሙ የተለያዩ ማኅበረሰብ አቀፍ ጤናነክ ሥራዎችን በመሥራት ኀላፊነቱን ሲወጣም ቆይቷል።

ስር የሰደደ የጉበት በሽታን በተመለከተ በሽታው ያለበት የስርጭት ሁኔታ፣ አጋላጭ ምክንያቶች፣ የመከላከያ መንገዶች እና የግንዛቤ ፈጠራ ሥራን በተመለከተ ከተለያዩ ተቋማት ከተውጣጡ የዘርፉ ባለሙያዎች ጋር የምክክር መድረክ በደሴ ከተማ አካሂዷል።

የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ ላይ በጥንካሬ ባለመሠራቱ እና ከህክምና ባለሙያዎች ዕውቅና ውጭ የባሕል መድኃኒቶችን ያለአግባብ በመውሰድ ብዙ ታማሚዎች በሽታው የማይድን ደረጃ ሲደርስ ብቻ ወደ ህክምና ተቋማት እንደሚመጡ በመድረኩ ተመላክቷል።

አሚኮ ያነጋገራቸው በበሽታው ዙሪያ ጥናት እና ምርምሮችን ያካሄዱ ምሁራን እንደተናገሩት መሰል የምክክር መድረኮች አስፈላጊ መኾናቸውን በማውሳት በበሽታው ዙሪያ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሠራ ይገባል።

የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ደሴ ቅርንጫፍ ዋና ዳይሬክተር አንተነህ ደመላሽ ተቋሙ የተለያዩ ማኅበረሰብ አቀፍ የጤና ሥራዎችን ሢሠራ መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡

ዳይሬክተሩ በዚህ የውይይት መድረክ ስር የሰደደ የጉበት በሽታን አስከፊነት እና ሊወሰዱ በሚገቡ የመከላከል እርምጃዎች ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር መግባባት ላይ መደረሱን ተናግረዋል፡፡

በውይይት መድረኩ የጉበት በሽታን በተመለከተ የቅድመ መከላከል ሥራዎችን በመሥራት እና በማኅበረሰቡ ዘንድ ከመቼውም ጊዜ በላይ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራን በተገቢው መልኩ በመከወን የጉበት በሽታ ስርጭትን መግታት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ምክክር ተደርጓል።

ዘጋቢ፡- ደምስ አረጋ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበቀጣይ ዓመት ሕጻናት ከትምህርት ቤት እንዳይቀሩ ኅብረተሰቡ የድርሻውን እንዲወጣ ትምህርት ቢሮ ጠየቀ፡፡
Next article“ተሳትፏዊ ግብርና እና የአየር ንብረት ሽግግር” መርሐ ግብር ይፋ ተደረገ፡፡