በቀጣይ ዓመት ሕጻናት ከትምህርት ቤት እንዳይቀሩ ኅብረተሰቡ የድርሻውን እንዲወጣ ትምህርት ቢሮ ጠየቀ፡፡

17

ባሕር ዳር፡ ሰኔ 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ በቀጣይ የትምህርት ሥራዎች ዙሪያ ከሚዲያ መሪዎች እና ባለሙያዎች ጋር የጋራ የምክክር መድረክ አካሂዷል።

በመድረኩ የክልሉ ከፍተኛ የሥራ መሪዎች፣ የተቋማት የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊዎች፣ የመገናኛ ብዙኃን መሪዎች፣ ባለሙያዎች እንዲሁም ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

በመድረኩ የተገኙት የትምህርት ቢሮ ምክትል ኀላፊ መኳንንት አደመ በክልሉ አንድ ዓመት ሊያስቆጥር ወራት በቀሩት የሰላም እጦት ምክንያት አንዳንድ አካባቢዎች እድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ሕጻናት ምንም በማያውቁት ምክንያት ከትምህርት ገበታቸው ሳይገኙ ቀርተዋል ብለዋል።

ያለ ሰላም ትምህርት የማይታሰብ እንደኾነ የገለጹት ምክትል ኀላፊው ችግሩ እንዳይደገም ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የትምህርት ተቋማትን የፖለቲካ ማዕከል አድርጎ የሚሠራ የጽንፈኝነት አስተሳሰብ እንደ ሕዝብ ለዘመናት የማንወጣው አዘቅት ውስጥ የሚከት ነው ብለዋል፡፡

በትውልድ ቅብብሎሽ ውስጥ መጥፎ ታሪክ እንዲጻፍ የሚያደርግ እኩይ ድርጊት ስለመኾኑም አብራርተዋል፡፡

የትምህርት ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ጌታቸው ቢያዝን የትምህርት ሥርዓቱ በተለያዩ ምክንያቶች ስብራት አጋጥሞታል ብለዋል፡፡

አቶ ጌታቸው ይሄን ፈተና ለማለፍ የሚዲያ እና የኮሙዩኒኬሽን ሚና ከፍተኛ በመኾኑ አሁናዊ የትምህርት ስብራቱን ለመጠገን በጋራ መረባረብ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በመድረኩ የተገኙት የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኀላፊ መንገሻ ፈንታው (ዶ.ር) “ትምህርት ላይ ካልተሠራ እንደ ሀገር ወደኋላ እንቀራለን” ብለዋል።

የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ እንዳለው ትምህርት ላይ ያልሠራ ሀገር እና ሕዝብ ከችግሩ መውጣት የማይችል እና የትውልድ ቅብብሎሹም ባልተለወጠ ትውልድ መካከል ይኾናል ነው ያሉት ዶክተር መንገሻ።

ይህ እንዳይኾንም የሚዲያ እና ኮሙዩኒኬሽን ሥራ ዋና ግቡ ትውልድ ማነጽን ማዕከል ያደረገ መኾን እንዳለበት አስገንዝበዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በአቅም ግንባታ ረገድ ከሩሲያ፣ ከሕንድ፣ ከቻይና እና ከተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች ጋር በትብብር ለመሥራት ምክክር ተካሂዷል” የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ቴዎድሮስ ምኅረት
Next articleየጉበት በሽታ አንዱ የማኅበረሰብ ስጋት በመኾኑ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሠራ እንደሚገባ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አሳሰበ፡፡