
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ) አቶ አዳነ መስፍን በንግድ ሥራ የሚተዳደሩ የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ ናቸው።የመኖሪያ አካባቢያቸው ረግረጋማ በመኾኑ ብዙ ሰው በወባ እንደሚታመም ነግረውናል።
አቶ አዳነ የአልጋ አጎበር ይጠቀሙ እንደኾነ ስንጠይቃቸው “ከቀበሌ በቤተሰብ ብዛት የተሰጠን አጎበር ቢኖርም ለሰውነት አላርጂክ ይፈጥራል በሚል እስካሁን አልተጠቀምንበትም፤ አሁን ግን ቤተሰቤ በሙሉ በተደጋጋሚ በወባ ስለታመመ ለመጠቀም እያዘጋጀነው እንገኛለን” ብለዋል።
በባሕር ዳር ዙሪያ ወራሚት ሦስቱ ቀበሌ ገበሬ ማኅበር ነዋሪ የኾኑትን አርሶ አደር በለው እዳየሁን ያገኘናቸው በአጎበር ከሸፈኑት የጤፍ ገለባ እየመዘዙ ከብቶቻቸውን ሲመግቡ ነው።
እኛም ራሳችንን ካስተዋወቅናቸው በኋላ የገለባ ክምሩን በምን እንደሸፈኑት ጠየቅናቸው። እርሳቸውም ” ገለባውን አሞራ እየጫረ ሲያስቸግረኝ ዛንዚራ አለበስሁት፤ በዛንዚራ የተሸፈነውን ገለባ አሞራው አይደፍረውም” በማለት ነገሩን።
አርሶ አደሩ አክለውም “በመኸር ወቅት የጤፍ፣ የኑግ፣ የአተር እና የባቄላ ገለባውን ከአውድማ ወደ መንደር የምናመጣው በዛንዚራው ጠቅልለን ነው ” አሉን። ዛንዚራውን መንግሥት በነጻ የሰጣቸው የወባ በሽታን እንዲከላከሉበት ይሁን እንጅ ለተባለው አላማ ሲያውሉት ግን አልተስተዋለም፡፡
በምዕራብ ጎጃም ዞን ፍኖተ ሰላም ከተማ የሚኖሩት ወይዘሮ ቦሰና መኮንን የአልጋ አጎበር ባለማግኘታቸው እስከ ቤተሰባቸው ለወባ በሽታ እንደተዳረጉ ተናግረዋል።
የፍኖተ ሰላም ከተማ አሥተዳደር ጤና ጣቢያ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይሁኔ ያለውም የአልጋ አጎበርን ላላስፈላጊ ጥቅም የሚያውሉ እንዳሉ ሁሉ አጎበር ፈልገው ባለማግኘታቸው ለበሽታ የተዳረጉ በርካታ ዜጎች ስለመኖራቸው ነው የሚናገሩት፡፡
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ጤና መምሪ ኀላፊ ዓለም አሰፋ ኅብረተሰቡ የወባ የመከላከያ ዘዴዎችን ቸል በማለቱ በሽታው በብዛት በከተማዋ መታየቱን ገልጸዋል፡፡
” በዋናነት” አሉ ኀላፊዋ ኅብረተሰቡ ያለውን የወባ ትንኝ መከላከያ የአልጋ አጎበር በአግባቡ የመጠቀም ችግር ይስተዋልበታል። ሌላው ደግሞ የወባ መራቢያ ተብለው የተለዩ ቦታዎችን ከማጽዳት፣ ውኃ ያቆሩ ጉድጓዶችን ከማዳፈን፣ የሚፋሰሱ ቦታዎችን ከመክፈት አኳያ ድክመት አለ። ይህም ኾኖ መንግሥት የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ እየሠራ ሲኾን ህክምናም እየተሰጠ ነው ብለዋል።
የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በላይ በዛብህ ሰሞኑን በሰጡት መግለጫ የወባ በሽታ በክልሉ ከፍተኛ ችግር ኾኗል ብለዋል።
ዳይሬክተሩ አያይዘውም በበጀት ዓመቱ ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የወባ በሽታ ሕክምና ማግኘታቸው የበሽታውን የስርጭት ስፋት እንደሚያሳይ ገልጸዋል።
እየገባ ባለው የክረምት ወቅትም ከፍተኛ የወባ በሽታ ሊያጋጥም ስለሚችል ወረርሽኝ ተከስቶ የሰው ሕይዎት እንዳይጠፋ በትኩረት መሥራት ይጠበቃል ነው ያሉት።
ዳይሬክተሩ ጨምረው እንዳብራሩት በ2016 በጀት ዓመት ከ3 ሚሊዮን በላይ የአልጋ አጎበር በክልሉ በተመረጡ ወረዳዎች መሠራጨቱን ተናግረው፤ ኅብረተሰቡም የአልጋ አጎበርን በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባው አመላክተዋል፡፡
በተመረጡ አካባቢዎችም የጸረ ወባ ትንኝ ርጭት ለማካሄድ መታቀዱንም ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል፡፡
የክልሉ ጤና ቢሮ ኀላፊ አቶ አብዱልከሪም መንግሥቱ በክልሉ በወባ የሚታመሙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ጠቁመው ኅብረተሰቡ የመከላከያ ዘዴዎችን በአግባቡ በመጠቀም ራሱን ከወባ በሽታ እንዲጠብቅ ጠይቀዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!