
ባሕር ዳር: ሰኔ 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ከፍተኛ መሪዎች በክልሉ ወቅታዊ የሰላም፣ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ሥራዎች አፈጻጸም ዙሪያ ውይይት አካሂደዋል፡፡
በአማራ ክልል የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ ፓርቲያችን ለሰላም ቅድሚያ የሚሰጥና ዘላቂ ሰላምን በውይይት ለማምጣት አልሞ ለመሥራት የሚያስችል እሳቤ ያለው ፓርቲ ነው ብለዋል።
የፓርቲው ሰላም ፈላጊነት በወቅታዊ ሁኔታዎች የተንጠለጠለ ሳይኾን በፓርቲ ፕሮግራም ላይ በግልጽ ለሰላም በትጋት እንደሚሠራ ያስቀመጠና ለተግባራዊነቱም ከላይ እስከታች ያለው አመራር በቁርጠኝነት እየሠራበት ያለ ቁልፍ ተግባር ስለመኾኑ አቶ ይርጋ ተናግረዋል፡፡
ዘላቂ ሰላም የመፍጠር ሥራ በቅንጅት መሠራት ያለበትና የሁሉንም ባለድርሻ አካላት የጋራ ጥረት የሚጠይቅ ተግባር ነው ብለዋል፡፡
በድጋፍና ክትትል ሥራው የተገኙ መልካም ተሞክሮዎች በቀጣይነት በማስፋት የሕዝባችንን ተጠቃሚነትና ብልጽግና ለማረጋገጥ በትጋት እንሠራለን ነው ያሉት አቶ ይርጋ።
በጊዜ የለንም ስሜት በጋራና በቅንጅት በመሥራት በክትትልና ድጋፉ የተለዩ ክፍተቶችን ለመቅረፍ መሥራት እንደሚገባ ማሳሰባቸውን ከአማራ ብልጽግና ፓርቲ ማኅበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!