
ደብረ ብርሃን: ሰኔ 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በግብይት ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ በሰሜን ሸዋ ዞን እና ደብረ ብርሃን ከተማ ለሚገኙ ሸማች ኅብረት ሥራ ማኅበራት፣ ለጅምላ ነጋዴዎች እና ለባለድርሻ አካላት የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ሥልጠና ሰጥቷል።
የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ምክትል ኀላፊ ብዙዓለም ግዛቸው በቂ የገበያ ትስስር አለመኖር፣ የግንዛቤ እጥረት እና የገበያ መሠረተ ልማት ደካማ መኾን የክልሉን የንግድ እንቅስቃሴ በተፈለገው መንገድ እንዳይቀጥል ስለማድረጉ ነው ያብራሩት።
በሸማች እና በምርት መካከል ያለውን የንግድ ሰንሰለት በማሳጠር ጤናማ ግብይት እንዲኖር መሥራት ይገባል ብለዋል።
የሥልጠናው ተሳታፊዎችም የካፒታል ውስንነት እና የመሸጫ ቦታ ችግሮች መኖራቸውን ጠቅሰው የተሳለጠ የንግድ እንቅስቃሴ እንዲኖር የባለድርሻ አካላት ድጋፍ እና እገዛ ይጠይቃል ነው ያሉት።
የሰሜን ሸዋ ዞን ንግድ እና ገበያ ልማት መምሪያ ፈጠነ ሞገስ (ዶ.ር) ዞኑ ከ 61 ሚሊዮን ብር በላይ ለገበያ ማረጋጊያ መመደቡን ገልጸው እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን ለመፍታትም እንደሚሠራ ነው ያስገነዘቡት።
የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ንግድ እና ገበያ ልማት መምሪያ ኀላፊ ይርጋለም ምሥጋናው አዳዲስ የገበያ ማዕከላትን የማስፋፋት ሥራዎች ላይ ትኩረት ተደርጎ እንደሚሠራ ጠቁመዋል፡፡ በበጀት ዓመቱ 26 ሚሊዮን ብር ለገበያ ማረጋጊያ ሥራ ላይ መዋሉንም አብራርተዋል።
የማኅበረሰቡን ፍላጎት ለማርካትም ተጨማሪ የንግድ አሠራር ሥርዓት እና መሠረተ ልማቶችን የመዘርጋት ተግባራት እንደሚቀጥሉም ነው የተገለጸው።
ዘጋቢ፡- በላይ ተስፋዬ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!