“በዞኑ 82 የንፁህ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክቶች ተጠናቅቀው ለኅብረተሰቡ አገልግሎት እየሰጡ ነው” የሰሜን ወሎ ዞን

18

ባሕር ዳር: ሰኔ 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜን ወሎ ዞን በበጀት ዓመቱ 11 ወራት 82 የንፁህ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክቶች ተጠናቅቀው ለኅብረተሰቡ አገልግሎት እየሰጡ መኾኑን የሰሜን ወሎ ዞን ውኃ እና ኢነርጂ መምሪያ ኀላፊ ፋሲል አረጋ ገልጸዋል። በበጀት ዓመቱ የዞኑን የመጠጥ ውኃ አቅርቦት ለማሳደግ እና ለማስፋፋት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየተሠራ መኾኑን ነው ያብራሩት፡፡ አቶ ፋሲል በበጀት ዓመቱ 110 የንፁህ መጠጥ ውኃ ተቋማትን ለመገንባት ታቅዶ በ11 ወር አፈጻጸም 82 ሲጠናቀቁ በበጀት ዓመቱ ቀሪ ጊዜ 34ቱን ለማጠናቀቅ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

በ2016 በጀት ዓመት ግንባታቸው ተጠናቅቆ አገልግሎት እየሰጡ ካሉት 82 የንፁህ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክቶች 52 ሺህ 551 ዜጎች ተጠቃሚ ስለመኾናቸው አስረድተዋል፡፡ መምሪያው በ2015 በጀት ዓመት ከተበላሹ 809 የውኃ ተቋማት 405ቱ በተያዘው በጀት ዓመት ተጠግነው አገልግሎት እንዲሰጡ መደረጉን ገልጸዋል፡፡ አቶ ፋሲል ቀሪዎቹ 404 ተቋማትን ጠግኖ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ የአጋር አካላትን ድጋፍ እንደሚፈልግ ተናግረዋል።

የሰሜን ወሎ ዞን የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ እንደገለጸው በቀጣዩ በጀት ዓመት የንጹህ መጠጥ ውኃ አቅርቦትን ለማሳደግ በልዩ ትኩረት እንደሚሠራ ጠቁመዋል፡፡ መምሪያው የ11 ወር አፈፃፀሙን ከወረዳ ማኔጅመንት አባላት ጋር በወልድያ ከተማ ገምግሟል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየ6ኛ ክፍል ክልል አቀፍ ፈተና መጠናቀቁን ትምህርት ቢሮ ገለጸ፡፡
Next article“በሸማች እና በምርት መካከል ያለውን የንግድ ሰንሰለት በማሳጠር ጤናማ ግብይት እንዲኖር መሥራት ይገባል” ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ