
ባሕር ዳር: ሰኔ 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የልብ ህመም የልብ ጡንቻ፣ የልብ ቧንቧ መሸፈኛ ወይም የልብ የደም ስሮች በተለያዩ ምክንያት ጉዳት ሲያጋጥማቸው የሚከሰት ችግር ነው። የልብ ችግር በተፈጥሮ የሚከሰት ሲኾን በሕጻናት ላይ ይበልጥ ጎልቶ እንደሚታይ መረጃዎች ያሳያሉ። የልብ ህመም በተለይም ደግሞ የልብ ደም ስር ህመም በታዳጊ ሀገራት ላይ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ እና የማኅበረሰብ ችግር እየኾነ ይገኛል። ኢትዮጵያ ውስጥም ህመሙ እየጨመረ ይገኛል።
በአማራ ክልል ጤና ቢሮ የህክምና እና ተሃድሶ አገልግሎት ዳይሬክተር ዶ/ር ማረው ጌጡ እንዳሉት የልብ ህክምና በክልሉ በሚገኙ በ28 የመንግሥት እና የተሻለ ደረጃ ባላቸው የግል ሆስፒታሎች መሰረታዊ የልብ ህክምና ትምህርት በወሰዱ የውስጥ ደዌ ህክምና ስፔሳሊስት ሐኪሞች አገልግሎት እየተሰጠ ነው።
ይሁን እንጅ አገልግሎቱ ዘመኑን በሚመጥን መሳሪያ እና በሠለጠነ የሰው ሃይል የመስጠት ችግሮች መኖራቸውን አንስተዋል። በተለይም ደግሞ የሕጻናት ህክምና በክልሉ ተደራሽ አለመኾኑን ነው ያነሱት። አብዛኛዎቹ ታካሚዎችም በአዲስ አበባ እና በውጭ ሀገራት እንዲሠራላቸው እየተደረገ መኾኑን አንስተዋል።
በቀጣይ አምስት ዓመታት በመድኃኒት የሚሰጠውን ህክምና ጨምሮ የቀዶ ጥገና አገልግሎትን በተደራጀ መንገድ ለመስጠት የሚያስችል የልብ ህክምና ማዕከላትን በባህርዳር በጎንደር፣ እና በደሴ ሆስፒታሎች ለሟቋቋም ስትራቴጅክ ፍኖተ ካርታ መዘጋጀቱን ዶ/ር ማረው ገልጸዋል። ህክምናውን በተሟላ መንገድ ለመስጠት ደግሞ በሙያው የሠለጠነ የሰው ሃይል ለማፍራት፣ ዘመኑን የሚመጥኑ የህክምና መሳሪያዎችን እና አገልግሎቱን መስጠት የሚያስችሉ መሠረተ ልማቶችን ለማሟላት የሚያስችሉ ሥራዎች እየተሠሩ ነው።
አሁን ላይ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል እና ጥበበ ጊዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ባለሙያዎችን እያሠለጠኑ መኾኑን ገልጸዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!