
ባሕር ዳር: ሰኔ 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የአማራ ክልል ከፍተኛ መሪዎች በሰላም እና በልማት ሥራዎች ዙሩያ ተወያይተዋል፡፡ በውይይቱ ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ፣ የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ፣ በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል፡፡
በውይይቱ የተሳተፉ መሪዎችም ሕዝብ ሰላም እንዲኾን እየጠየቀ መኾኑን ተናግረዋል፡፡ የአማራ ክልል ሴቶች ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትል ኀላፊ ንፁሕ ሽፈራው ከፍተኛ መሪዎች ስምሪት ተሰጥተው ድጋፍ እና ክትትል ሲያደርጉ መቆየታቸውን ገልጸዋል፡፡ ከሕዝብ ጋር ተደጋጋሚ ውይይት በመደረጉ እና የጸጥታ ኀይሉ በሠራው ሥራ በክልሉ አንጻራዊ ሰላም መገኘቱንም ተናግረዋል፡፡
የመሪዎች ስምሪት ዋና ተግባሩን ያደረገው በዘላቂነት ሰላምን የማስፈን ሂደቱ ታች ድረስ እግር መትከል ላይ መኾኑንም አንስተዋል። በተሰጠው ተልዕኮ አማካኝነት በርካታ ሥራዎች መሠራታቸውንም አስገንዝበዋል፡፡ መሪዎች በዘላቂነት ሰላምን ለማስፈን በተደጋጋሚ ውይይት ማድረጋቸውንም አንስተዋል፡፡
ማኅበረሰቡ በሰላም ወጥቶ መግባት፣ ልማት ማልማት የሚችልበትን ሁኔታ ለመፍጠር ሥራዎች መሠራታቸውንም አመላክተዋል፡፡ ከሕዝብ ጋር በተደረጉ ተደጋጋሚ ውይይቶች መጀመሪያ ኾኖ የሚቀርበው ሰላም እንዲረጋገጥ መኾኑንም አንስተዋል፡፡ ሰላምን ማምጣት የሚቻለው በመንግሥት ጥረት ብቻ አለመኾኑንም ገልጸዋል፡፡
ውይይት በማድረግ፣ በመቀራረብ እና በመነጋገር ዘለቂ ሰላም እንዲመጣ የሕዝብ ፍላጎት ነው ብለዋል፡፡ በጸጥታ ችግር ምክንያት ያሉ ሕገወጥ ተግባራት እንዲቆሙለት ሕዝቡ እንደሚፈልግም ተናግረዋል፡፡ በሕዝባዊ ውይይቶች የኑሮ ውድነት እንዲቀንስ፣ ልማት እንዲፋጠን፣ አገልግሎት አሰጣጥ የተሟላ እንዲኾን ይጠይቃልም ነው ያሉት፡፡
የመሪዎች ስምሪትም የሕዝብ ጥያቄዎችን ለመፍታት እና ችግሮችን ለማስተካከል ነው ብለዋል፡፡ በክልሉ በሁሉም አካባቢዎች የልማት ሥራዎች በጥሩ ሁኔታ እየተጀማመሩ መኾናቸውን ነው ያነሱት፡፡ በየከተሞች የተጀመሩ የከንቲባ ችሎቶች የሕዝብን ችግር እያደመጡ እየፈቱ መኾናቸውንም ነው የተናገሩት፡፡
የአማራ ክልል ትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ባለሥልጣን ዳይሬክተር ዘውዱ ማለደ በድጋፍ እና በክትትሉ መልካም ነገሮችን ማየታቸውን ነው የገለጹት፡፡
ሕዝቡ ሰላሙን በራሱ አቅም እየጠበቀ፣ ለሰላም ችግር የኾኑ አካላትን ለጸጥታ ኀይሉ እያጋለጠ ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ እየሠራ ነው ብለዋል፡፡ ሕዝቡ የጸጥታ መዋቅሩን የማጠናከር፣ የመደግፍ ሥራ እየሠራ መኾኑንም አንስተዋል፡፡ የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች በውይይት መፈታት አለባቸው እያለ ነው፣ መንግሥት ከዚህም በላይ እጁን ለሰላም እንዲዘረጋ ግፊት እያደረገ መኾኑን ነው ያነሱት፡፡
ሕዝቡ ነፍጥ አንስተው ወደ ጫካ የገቡ ወገኖች እንዲመጡ ጥሪ እናደርጋለን፣ ወደ ሰላሙ እንዲመጡ በሽምግልና እና በሌሎች አማራጮች ግፊት እናደርጋለን፣ የራሳችንን ኀላፊነት እንወጣለን እያለም ነው ብለዋል፡፡ ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር በተደረገ ውይይት ለሰላም ቅድሚያ ሰጥቶ መሥራት እንደሚገባ አጽንኦት ተሰጥቶበታል ብለዋል፡፡
በርካታ የልማት ሥራዎች እየተገነቡ መኾናቸውንም አመላክተዋል፡፡ ከሰላም ጎን ለጎን የመልካም አሥተዳደር ችግሮች እንዲፈቱ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ በከንቲባ ችሎቶች እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች ፍትሕን እየሰጡ እና ሕዝብን እያስደሰቱ መኾናቸውንም አመላክተዋል፡፡ የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኀላፊ እንድሪስ አብዱ የተጀመሩ ሥራዎች እንዲጠናቀቁ ከመሪዎች ጋር መግባባት ላይ በመድረስ ከሕዝብ ጋር ሰፋፊ ውይይቶች መደረጋቸውን ተናግረዋል፡፡
ሕዝቡ የሚያነሳቸውን በርካታ ጥያቄዎች ሰላምን ከማስፈን ሥራ ጎን ለጎን ለመፍታት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር መወያየታቸውንም አንስተዋል፡፡ በተደረጉ ውይይቶች ሕዝቡ የሚያነሳው ሰላም እንዲረጋገጥለት ነው ብለዋል፡፡ ሕዝቡ ሰላም እንደሚያስፈልገው ብቻ ሳይኾን የሰላሙ ባለቤት እንደኾነም እንደሚያነሳ አስረድተዋል፡፡
የተጀመረውን ሰላም ለማጽናት፣ ያልተጀመሩ ሥራዎችን ለመጀመር መግባባት ፈጥረናል ብለዋል፡፡ ትኩረት ያልተሰጣቸው ሥራዎች ወደተሟላ ሥራ እንዲገቡ መደረጉንም ገልጸዋል፡፡ የልማት ሥራዎችን አጠናክረው እንደሚቀጥሉም አስታውቀዋል፡፡ አሁን ያለውን ከፍተኛ ቁጭት እና ግለት አጠናክሮ በመቀጠል መሥራት ይጠበቃልም ብለዋል፡፡
የአማራ ክልል ሥራ አመራር ኢኒስቲትዩት ፕሬዚዳንት እሱባለው መሰለ የጸጥታ ችግሩ ከተከሰተ ጀምሮ የማረጋጋት፣ የማጽናት እና እግር የመትከል ሥራዎች መሠራታቸውን ገልጸዋል፡፡ በተደረገው ሥምሪት ሰላሙን የማጠናከር እና የልማት ሥራዎችን የማፋጠን ሥራ መሠራታቸውን አንስተዋል፡፡ ከተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ጋር በተደረገ ውይይት ሰላም እንዲረጋገጥለት፣ መንግሥት ሕግ እንዲያስከብርለት ይፈልጋል ነው ያሉት፡፡
አሁን ያለው ሁኔታ ዘላቂ ሰላምን ስለማያረጋግጥ ሁሉም አካል ወደ ውይይት እንዲመጣ እና ሰላም እንዲመጣ ይፈልጋል ብለዋል፡፡ ተደናግረው የነበሩ የኅብረተሰብ ክፍሎችም ወደ ቀልባቸው ተመልሰው ችግሮችን በውይይት እንዲፈቱ ግፊት እያደረጉ መኾናቸውንም አመላክተዋል፡፡ ግጭትን በመሸሽ ልማት ፈላጊነት እና መደበኛ ሥራዎች እንዲቀጥሉ ግፊት እያደረገ ነው ብለዋል፡፡ የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች በውይይት እንጂ ራስን በራስ በማጥፋት መፍትሔ እንደማይመጣ እየተናገረ መኾኑንም አመላክተዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!