
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ እና የቻይና የንግድ እና ኢንቨስትመንት ትውውቅ መድረክ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው። በመድረኩ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ሃሰን መሐመድ፣ የገንዘብ ሚኒስትር ዴዔታ ሰመሪታ ሰዋሰው፣ የአዲስ አበባ ንግድ እና የዘርፍ ማኀበራት ምክር ቤት የሥራ ኅላፊዎች እና የቻይና የንግድ ምክር ቤት ልዑክ ተሳትፈዋል፡፡
አቶ ሃሰን መሐመድ በዚህ ወቅት እንደገለጹት ኢትዮጵያ እና ቻይና ለረጅም ዓመታት የዘለቀ የንግድ እና ኢንቨስትመንት ግንኙነት አላቸው። ሁለቱን ሀገራት ተጠቃሚ የሚያደርግ የንግድ እና ኢንቨስትመንት አማራጮችን በማስፋት በኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ በግብርና፣ በቴክኖሎጂ ልማት እና በሌሎች ዘርፎችም በጋራ በመሥራት ውጤታማ መኾናቸውን ገልጸዋል።
በቀጣይም ዜጎችን ተጠቃሚ በሚያደርጉ የንግድ እና ኢንቨስትመንት ትብብርን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ እና የዛሬው መድረክ አጋዥ እንደሚኾን ተናግረዋል። የቻይና ልዑካን ቡድን ተወካይ እና የሲፒሲ ምክትል ፀሐፊ ሊዩ ዋይ በበኩላቸው ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የቆየ የልማት ትብብር አጠናክራ ለመቀጠል ትሠራለች ብለዋል፡፡
ኢዜአ እንደዘገበው የቻይና ባለሃብቶች በኢትዮጵያ በኮንስትራክሽን ፣ በኢንዱስትሪ እና በግብርናው ዘርፍ በስፋት በመሰማራት ለበርካታ ዜጎች የሥራ እድል እየፈጠሩ መኾኑን አንስተዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!