የመንግሥት ሠራተኞች የደረጃ እድገት እና የእርከን ጭማሪ በአዲሱ ረቂቅ አዋጅ ተፈቅዷል ተባለ።

241

ባሕር ዳር: ሰኔ 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ) አዲሱ የፌዴራል መንግሥት ረቂቅ የሠራተኞች አዋጅ ሠራተኞች ተመዝነው በአፈጻጸማቸው የሚለዩበት እንደኾነ የፌደራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኮሚሽነር መኩሪያ ኃይሌ (ዶ.ር) ገልጸዋል። አዋጁን በተዛባ መንገድ መረዳት አይገባም ያሉት ኮሚሽነሩ አንድ ሠራተኛ ሁለት ጊዜ ተመዝኖ ውጤቱ ከመካከለኛ በታች ከኾነ ከሥራው እንደሚሰናበትም ጠቁመዋል።

በዚህ ምዘና በቂ ውጤት ያመጡ ሠራተኞች ደግሞ የደረጃ እድገት እንዲሁም በየሁለት ዓመቱ የሚኖር የእርከን ጭማሪ እንዲያገኙ በአዋጁ ተደንግጓል ብለዋል። የአዋጁ ዋና ዓላማ ሠራተኛን መቀነስ ሳይኾን ማብቃት ነው ያሉት ዶክተር መኩሪያ ኃይሌ በምዘናው ደረጃ አሟልተው ብቁ የኾኑ፣ የተወሰነ ክፍተት ያለባቸው እና ሰፋ ያለ ክፍተት የታየባቸው ተለይተው ክፍተቶቹ በሥልጠና እየተሟሉ ሦስቱም በመንግሥት መዋቅር ውስጥ የሚቀጥሉ ናቸው ብለዋል።

የመንግሥት ሠራተኛው በሥራው ተመጣጣኝ ገቢ አለማግኘቱ በኑሮው ላይ ጫና ፈጥሮበታል፤ አዋጁ ይህን ችግር ለመፍታት የሚያስችል ነው ወይ ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ማብራሪያም አዋጁ የብቃት ምዘናውን ያለፉ እና መስፈርቱን የሚያሟሉ ሠራተኞች የደሞዝ ጭማሪ በእርከን እና በደረጃ ዕድገት እያገኙ የሚሄዱበትን አስገዳጅ አሠራር መደንገጉን ተናግረዋል።

አዋጁ የፐብሊክ ሰርቪስ አገልግሎትን ለማሻሻል እና ዲጅታል ሲቪል ሰርቪስን ለመፍጠር ዓላማ ያደረገ ነው ያሉት ኮሚሽነሩ ሁሉም ብሔረሰብ የተማረ የሰው ኃይል አለው ተብሎ ስለሚታሰብ ብዝኅነትን መሠረት ያደረገ ፕብሊክ ሰርቪስ ለመገንባት መታሰቡን ተናግረዋል። ሥራ ላይ ያለው የፌዴራል መንግሥት የሠራተኞች አዋጅ ፖሊሲን መሠረት አድርጎ የተቀረጸ አይደለም ያሉት ኮሚሽነሩ የመንግሥት አገልግሎትን መሠረታዊ በኾነ መልኩ ለመቀየር የሚያስችልም አልነበረም ብለዋል።

አሁን የተዘጋጀው አዋጅ ነጻ እና ገለልተኛ ሲቪል ሰርቪስ ለመገንባት፣ የሠራተኛውን ብቃት ለማረጋገጥ፣ ብዘኅነት እና አካታችነትን በተገቢው መንገድ ለመምራት እንደሚረዳ ዶክተር መኩሪያ ኃይሌ ገልጸዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በተገኘው አንጻራዊ ሰላም የተሟላ የፍትሕ አገልግሎት ለመስጠት እየሠራሁ ነው” የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር
Next article“ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የቆየ የልማት ትብብር አጠናክራ ለመቀጠል ትሠራለች”ሊዩ ዋይ