” ከችግር ለመውጣት ተስማምተን እና አንድ ኾነን መሥራት መቻል አለብን” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ

51

ባሕር ዳር: ሰኔ 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ከፍተኛ መሪዎች ውይይት እየተካሄደ ነው። በውይይቱ ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ፣ የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ፣ በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።

በውይይቱ መልዕክት ያስተላለፉት ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ጊዜው የመሪዎችን ቁርጠኝነት እንደሚፈልግ ገልጸዋል። ፈተና የበዛባቸው ወቅቶች ቁርጠኝነትን እንደሚፈጥሩም ተናግረዋል። የመሪዎች ቁርጠኝነት የሚገለጸው በተግባር መኾኑንም አመላክተዋል። በቁርጠኝነት ለመታገል መዘጋጀት እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል።

መሪዎች ድጋፍ እንዲያደርጉ እና ችግሮችን እንዲለዩ ወደ ዞኖች አሠማርተው እንደ ነበር ያነሱት ርእሰ መሥተዳድሩ በሁሉም ዘርፍ ድጋፍ እንዲያደርጉ የተላኩ መሪዎች ችግር በመለየት ችግር እንዲፈቱ ሚና ተሰጥቶቿው እንደነበር ገልጸዋል። መሪዎች የተቀመጡ አቅጣጫዎች እንዴት እየተተገበሩ እንደኾነ እንዲገመግሙ ማሠማራታቸውንም አስታውሰዋል።

የመሪዎችን ቆይታ መገምገም እና የወደፊት የሥራ አካል አድርጎ መሥራት እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል። ተልዕኮ እና አቅጣጫ ይዞ የሄደው መሪ ተልዕኮውን ማስረከብ እንደሚያስፈልግ ነው ያመላከቱት። የገጠመውን ችግር በመፍታት እና በማስተካከል ቀደም ሲል የነበሩ መደበኛ ሥራዎች እንዴት እየሄዱ እንደኾነ እንደሚገመግሙም ገልጸዋል።

በአስተሳሰብ እና በአተገባበር ሂደት የተደራጀ አካሄድ ስለመኖሩም እንደሚገመግሙ ተናግረዋል። ከታችኛው መዋቅር እስከ ላይኛው መዋቅር ድረስ የተግባር አንድነትን ማጠናከር፣ በተገቢው መንገድ መምራት ይገባል ብለዋል። በላይኛው እና በታችኛው መዋቅር ያለውን ግንኙነት ማስተካከል እና አንድ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ነው ያመላከቱት።

ከፍተኛ መሪዎች የሚሠሯቸው ሥራዎች በመካከለኛ እና በዝቅተኛ መሪዎች ተጽዕኖ እንዳለው ነው የተናገሩት። የላይኛው መዋቅር በተገቢው መንገድ መሥራት እንደሚገባውም አስገንዝበዋል። እያለቀ ባለው በጀት ዓመት በተፈጠረው ችግር ምክንያት በርካታ ሥራዎች መደነቃቀፋቸውን የገለጹት ርእሰ መሥተዳደሩ መሥራት የሚገባንን ባለ መሥራታችን ተሻጋሪ ችግር እንዲፈጠር ኾኗል ነው ያሉት።

ተሻጋሪ ችግሮችን በክረምቱ ወቅት መቀነስ እንደሚገባም ተናግረዋል። በችግሮች ላይ መነጋገር፣ አቅጣጫ ማስቀመጥ እና ለመፍታት መረባረብ ይገባናል ነው ያሉት። በክልሉ የሚነሱ ችግሮች እንዲፈቱ ኀላፊነቱ የተጣለው በክልሉ መሪዎች ላይ መኾኑንም ተናግረዋል። በክልሉ እና ከክልሉ ውጭ ያሉ ችግሮችን አይመለከተኝም ብለን ልንተወው አንችልም፣ አማራጫችን መጋፈጥ ነው ብለዋል።

ችግሮችን ለመጋፈጥ ደግሞ በዕውቀት ላይ በመመሥረት የኀይል ሚዛንን እያስጠበቁ ሥራዎችን መሥራት እንደሚጠበቅም አመላክተዋል። ችግሮችን ለመፍታት የሚቻለው በትብብር መኾኑን አስገንዝበዋል። የሕዝብን ጥቅም እና መብት ለማስከበር የማይፈልግ የለም ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ ፍላጎታችንን በችሎታ ማሳካት ካልቻልን ፍላጎት ብቻውን ምንም ነው ብለዋል።

ፍላጎትን ወደ ተጨባጭ ተግባር ለመቀየር በአንድነት መሥራት ይጠበቃል ነው ያሉት። የሕዝብን ጥቅም ለማስከበር ከንግግር ያለፈ ተግባራዊ ሥራ መሥራት ይገባል ብለዋል። በተግባር ለሚሠራው ሥራ መግባባት እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል። በማይዋዥቅ ስሜት እና አቋም በመኾን ለሕዝብ ጥቅም መሥራት እንደሚጠበቅም ተናግረዋል። ከችግር ለመውጣት ተስማምተን፣ አንድ ኾነን መሥራት መቻል አለብን ነው ያሉት።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በማዕድን ዘርፍ ላይ እሴት ያልተጨመረበት የማዕድን ሃብት ወደ ውጪ እንዳይወጣ የሚል ሕግ እየተረቀቀ ነው” ኢንጂነር ሃብታሙ ተገኝ
Next article“በተገኘው አንጻራዊ ሰላም የተሟላ የፍትሕ አገልግሎት ለመስጠት እየሠራሁ ነው” የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር