የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን እና የሰላም ሚኒስቴር በጋራ ለመሥራት ተስማሙ።

21

ባሕር ዳር: ሰኔ 13/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን ባለሥልጣን ከሰላም ሚኒስቴር ጋር መገናኛ ብዙኀን ሰላምን ለማስጠበቅ ያላቸውን ሚና የሚያጠናክር የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርሟል፡፡

በፊርማ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር መሐመድ እድሪስ መገናኛ ብዙኀን ለሰፊው የሕብረተሰብ ክፍል ያላቸውን ተደራሽነት ተጠቅመው ሰላምን በማጠናከር ለሀገራዊ ግንባታ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወቱ ገልጸዋል።

ባለሥልጣኑ የጥላቻ ንግግር እና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከል እያከናወነ ባለው ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሐ ግብር ጥላቻን በመዋጋት አብሮነትን እና ሰላምን እያሰረጸ ይገኛል ብለዋል፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም መገናኛ ብዙኀን በሕግ የተሰጣቸውን ስልጣን እና ኀላፊነት በመጠቀም ለሰላም የሚቆረቆር ማኀበረሰብ ለመፍጠር የሚያደርጉትን ጥረት ለማገዝ የሁለቱ ተቋማት በጋራ መሥራት አስላጊ መኾኑን ገልጸዋል፡፡

በሰላም ሚኒስቴር የሰላም ግንባታ እና ብሔራዊ መግባባት ዘርፍ ሚኒስትር ድኤታ ከይረድን ተዘራ (ዶ.ር) በበኩላቸዉ ማኀረሰብ ላይ መሥራት የሚቻለው መገናኛ ብዙኀን የሰላም ሃሳቦች ላይ በማተኮር የተረጋጋ ሀገር ለመፍጠር አይነተኛ ሚና ሲጫወቱ ነው ብለዋል፡፡

ሚኒስትር ድኤታው አክለውም ከኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን ባለሥልጣን ጋር በጋራ መሥራታችን የሰላም ግንባታ ሂደትን ከማጠናከሩም በላይ ለሀገራዊ ደህንነት ያለው ፋይዳ የጎላ እንደሚኾን ገልጸዋል።

በስምምነቱ ወቅት ሁለቱ ተቋማት ሀገራዊ አንድነት እና ብሔራዊ መግባባትን ለማጠናከር የመገናኛ ብዙኀኑን አቅም ግንባታ ማጠናከር፣ ተደራሽነታቸውን ማረጋገጥ፣ ብዝሃነትን የሚያጠናክሩ ዘገባዎች ማቅረባቸውን መከታተል፣ የሐሰተኛ እና የጥላቻ ንግግሮችን ለመከላከል የሚያስችል የግንዛቤ መድረክ መፍጠር እንዲሁም በዘርፉ አስፈላጊ የኾኑ ጥናቶችን በጋራ መሥራት እንደሚኖርባቸው ተገልጿል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየልማት ሥራዎች እንዲጠናቀቁ አቅጣጫ ማስቀመጣቸውን ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ተናገሩ፡፡
Next article“የአገልግሎት አሰጣጣችንን ዘመናዊ እና ቀልጣፋ ለማድረግ ቴክኖሎጂን የሪፎርሙ መሠረት ማድረግ ይገባናል” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመሥገን ጥሩነህ