
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 13/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በባሕርዳር ከተማ እየተገነቡ የሚገኙ የልማት ሥራዎችን ተመልክተዋል፡፡
ርእሰ መሥተዳድሩ የባሕርዳር ዓለም አቀፍ ስታዲዬም፣ ጣና ዳርን የማስዋብ ፕሮጄክት እና በከተማዋ እየተገነቡ የሚገኙ ፕሮጄክቶች ከተመለከቷቸው የልማት ሥራዎች መካከል ናቸው፡፡
የባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው በዚህ ዓመት ተጠናቅቀው ለምርቃት መብቃት ያለባቸውን የልማት ሥራዎች ያሉበትን ሁኔታ ለማየት ዓላማ ያደረገ ምልከታ መደረጉን ገልጸዋል፡፡
ወደሚቀጥለው ዓመት የሚሸጋገሩ ፕሮጄክቶችን የእስካሁን ሥራዎች መጠበቅ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ አቅጣጫ መቀመጡንም አንስተዋል፡፡
ርእሰ መሥተዳድሩ በዓመቱ ማለቅ የሚገባቸው ፕሮጄክቶች በፍጥነት እንዲጠናቀቁ አቅጣጫ ማስቀመጣቸውን አስታውቀዋል፡፡ በተሰጠው መመሪያ እና አቅጣጫ መሠረት ይፈጸማሉም ብለዋል፡፡
ወደ ቀጣይ ዓመት የሚሸጋገሩ ፕሮጄክቶች በቀሪ ጊዜያት በተገቢው መንገድ እንዲሠሩ፣ በክረምት ወቅት ብልሽት እንዳይገጥማቸው ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባም አቅጣጫ ተቀምጧል ነው ያሉት፡፡
በሚቀጥለው ዓመት ያደሩ ፕሮጄክቶችን ከአዳዲስ ፕሮጄክቶች ጋር አስተባብሮ ለመምራት የሚያስችል መመሪያም መሰጠቱንም ተናግረዋል፡፡
ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የምልከታቸው ዓላማ በበጋ ወቅት ሲከናወኑ የነበሩ የልማት ሥራዎች ያሉበትን ደረጃ ለማየት መኾኑን ገልጸዋል፡፡
እየተሠሩ ያሉ የልማት ሥራዎች አንዳንዶቹ ወደ መጠናቀቂያ ደረጃ የደረሱ መኾናቸውንም ተናግረዋል፡፡ እስከ ሰኔ 30/2016 ዓ.ም ድረስ የሚጠናቀቁ ፕሮጄክቶች መኖራቸውንም አንስተዋል፡፡
የመጨረሻ ሥራዎች የሚቀራቸው ፕሬጄክቶች እንዲጠናቀቁ አቅጣጫ መስጠታቸውንም ገልጸዋል፡፡ ለሚቀጥለው ዓመት የሚሸጋገሩ ፕሮጄክቶች መኖራቸውን የተናገሩት ርእሰ መሥተዳድሩ ሲሸጋገሩ በዝናብ እና በጎርፍ ምክንያት እንዳይጎዱ ጥበቃ ማድረግ በሚገባቸው ዙሪያዎች ላይም ከባለሙያዎች ጋር መነጋገራቸውን ነው የተናገሩት፡፡
የክልሉ መሪዎች በሌሎች አካባቢዎች የልማት ሥራዎችን እየተመለከቱ መኾናቸውንም አስታውቀዋል፡፡ በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ምልከታ ሲያደርጉ ከቆዩ መሪዎች ጋር ውይይት እንደሚኖርም ተናግረዋል፡፡
ውይይቱ ግንባታዎችን በፍጥነት ማጠናቀቅ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ መኾኑንም አንስተዋል፡፡ “የሚመረቁትን እንመርቃለን፣ የሚከርሙትን ደግሞ በሚቀጥለው በጀት ዓመት የተሻለ በጀት መድበን ለማጠናቀቅ ጥረት እናደርጋለን” ነው ያሉት፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!