
ባሕር ዳር: ሰኔ 13/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በሰሜን ሽዋ ዞን ከመሐል ሜዳ ጦር መሣያ በሎት 1 እና ግሼ ራቤል ሚላሚሌ በሎት 2 ደረጃ 1 የአስፋልት መንገድ አስፋልት የማልበስ ሥራ ተጀምሯል። የመንገድ ሥራውን የቻይናው ዞንግሚ ኢንጅነሪንግ ግሩፕ በተቋራጭነት ይዞ እየሠራው ይገኛል፡፡
የአስፋልት ሥራው በፍጥነት እየተሠራ መኾኑን በቦታው ተገኝተው ያረጋገጡት የመንዝ ጌራ ምድር ወረዳ መሪዎች ተናግረዋል፡፡
መሪዎቹ መንገዱ በአጭር ጊዜ ሲጠናቀቅ የአካባቢውን ኢኮኖሚ በማነቃቃት የወረዳውን ዕድገት ከፍ እንደሚያደርገው አስተያየት ሰጥተዋል። በምልከታው የተገኙት የወረዳው ዋና አሥተዳዳሪ ኃይሌ የሺጥላ በበርካታ ተፅዕኖዎች ውስጥ ኾኖ ያለ እረፍት በተሻለ ፍጥነት እየሠራ ለሚገኘው የመንገድ ተቋራጭ ምሥጋና አቅርበዋል፡፡
የመንዝ ሕዝብ ቁልፍ ችግር የኾነው የጣርማ በር ሰፌድ ሜዳ መንገድ ተቋራጭ ተሞክሮውን በመውሰድ ሥራውን ለማስቀጠል እንደሚሠራ አስገንዝበዋል፡፡ የሰሜን ሽዋ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ እንዳለው የአካባቢውን ሰላም በማስጠበቅ የልማት ሥራዎችን ያለ እረፍት ለማስቀጠል ጥረት እንደሚደረግ አረጋግጠዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!