በምሥራቅ ጎጃም ዞን 107 ሚሊየን ችግኝ በወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት ለማስተከል ታቅዷል፡፡

14

ባሕር ዳር: ሰኔ 13/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የምሥራቅ ጎጃም ዞን የበጎ ፈቃድ አገልግሎት አሥተባባሪ ኮሚቴ በ2016 ዓ.ም የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ዙሪያ በደብረ ማርቆስ ከተማ ውይይት አካሄዷል። የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት እቅዱን ያቀረቡት የምሥራቅ ጎጃም ዞን ወጣቶች እና ስፖርት መምሪያ ኅላፊ ቢሻው ሞላ በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ600 ሺህ በላይ ወጣቶችን ለማሳተፍ መታቀዱን ገልጸዋል፡፡

በክረምቱ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተሳታፊዎች በደም ልገሳ፣ በማጠናከሪያ ትምህርት፣ በአካባቢ ጥበቃ፣ በትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ እና በሌሎች ዘርፎች ይሠማራሉ፡፡ በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት 468 የአቅመ ደካማ ቤቶችን የመጠገን እና 234 የአቅመ ደካማ ቤቶችን በአዲስ የመገንባት ተግባር ይከናወናል። በአረንጓዴ አሻራ 107 ሚሊየን ችግኝ በወጣቶች በጎ ፈቃድ ለማስተከል ታቅዷል ብለዋል፡፡

እንደ አቶ ቢሻው ሞላ ገለጻ በበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ 1 ሺህ 250 ዩኒት ደም ለማስለገስ የሚሠራ ሲኾን ወጣቶች የማጠናከሪያ ትምህርት በመስጠትም ይሳተፋሉ። የምሥራቅ ጎጃም ዞን ትምህርት መምሪያ ኅላፊ እና የማኀበራዊ ተቋማት ክላስተር አሥተባባሪ ጌታሁን ፈንቴ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሀገራቸውን የሚወዱ ዜጎች ተግባር በመኾኑ ዜጎችን በማሥተባበር በመንግሥት እና በሕዝብ ያልተሸፈኑ ተግባራትን በማከናወን የድርሻችንን ልንወጣ ይገባል ብለዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ለመሠረታዊ ማኅበራት ከደረሰው የአፈር ማዳበሪያ 90 በመቶ የሚኾነው ወደ አርሶ አደሩ ተሰራጭቷል” የአማራ ክልል ኅብረት ሥራ ማኅበራት ማስፋፊያ ባለሥልጣን
Next articleበመሐል ሜዳ እየተሠራ ያለው መንገድ የአስፋልት ማልበስ ሥራ ተጀመረ፡፡