“ለመሠረታዊ ማኅበራት ከደረሰው የአፈር ማዳበሪያ 90 በመቶ የሚኾነው ወደ አርሶ አደሩ ተሰራጭቷል” የአማራ ክልል ኅብረት ሥራ ማኅበራት ማስፋፊያ ባለሥልጣን

13

ባሕር ዳር: ሰኔ 13/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ለአማራ ክልል ለ2016/17 የምርት ዘመን 8 ሚሊዮን 57 ሺህ 900 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ግዥ ተፈጽሞ ወደ አርሶ አደሮች እየተሰራጨ ይገኛል። በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የማዳበሪያ አቅርቦቱን ተደራሽ ለማድረግ እየተሠራ መኾኑንም ተገልጿል። የግብዓት ተጠቃሚ ከኾኑት ውስጥ ደግሞ በሰሜን ጎጃም ዞን ባሕርዳር ዙሪያ ወረዳ ነዋሪ የኾኑት አርሶ አደር ዋለልኝ አንዳርጌ አንዱ ናቸው።

አርሶ አደር ዋለልኝ በ2016/17 የምርት ዘመን 8 ሄክታር መሬት በዘር ለመሸፈን እየሠሩ መኾኑን ነግረውናል። ለዚህ ደግሞ 6 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለመጠቀም አቅደዋል። እስከ አሁን ከሦስት ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ እና የበቆሎ ዘር ገዝቻለሁ ነው ያሉት።

አርሶ አደሩ ከሰው ሠራሽ የአፈር ማዳበሪያ ባለፈ 25 ኩንታል የተፈጥሮ ማዳበሪያ ጥቅም ላይ ማዋላቸውን ገልጸዋል። በዚህ ዓመት ግብዓትን ቀድሞ በማሰራጨት ባለፉት ዓመታት ከነበረው የተሻለ መኾኑን ያነሱት አርሶ አደር ዋለልኝ በቀጣይም ለሌሎች ሰብሎች ምርጥ ዘር እና ቀሪ የአፈር ማዳበሪያ በወቅቱ እንዲቀርብ ጠይቀዋል።

በሰሜን ጎጃም ዞን ኅብረት ሥራ ተጠሪ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አምሳሰው አቸነፍ እንዳሉት በ2016/17 የምርት ዘመን በዞኑ ለማቅረብ ከታቀደው 1 ሚሊዮን 164 ሺህ 864 የአፈር ማዳበሪያ ውስጥ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ የእቅዱ 62 በመቶ ቀርቧል ነው ያሉት። የቀረበውን የአፈር ማዳበሪያም ሙሉ በሙሉ ማሰራጨት ተችሏል ብለዋል። ከ30 ሺህ ኩንታል በላይ የበቆሎ ምርጥ ዘርም ወደ አርሶ አደሩ ተደራሽ መኾኑን ነው የጠቆሙት።

በክልሉ በተለያዩ ምክንያቶች ግብዓት ዘግይቶ ከገባባቸው ዞኖች ውስጥ አንዱ ሰሜን ጎጃም ዞን እንደነበር ያነሱት ኀላፊው በሥርጭት ሂደቱ አርሶ አደሩ ባለቤት ከመደረጉ ባለፈም ባለፈው ዓመት የታዩ ችግሮችን በመቅረፍ የቀረበውን ግብዓት ሙሉ በሙሉ ማሰራጨት ተችሏል ነው ያሉት። በቀጣይ ቀሪ ጊዜያት ግብዓት እንደቀረበ ወደ አርሶ አደሮች ፈጥኖ ተደራሽ እንደሚኾንም ገልጸዋል።

የአማራ ክልል ኅብረት ሥራ ማኅበራት ማስፋፊያ ባለሥልጣን ዋና ኀላፊ ጌትነት አማረ እንዳሉት በ2016/17 የምርት ዘመን ግዥ ከተፈጸመው ግብዓት ዘገባው እስከተጠናቀረበት ጊዜ 64 በመቶው ዩኒየኖች ላይ ቀርቧል። ከዚህ ውስጥ 92 በመቶው ወደ መሠረታዊ ማኅበራት ደርሷል፤ ከዚህ ውስጥ ደግሞ 90 በመቶ የሚኾነው ወደ አርሶ አደሩ ተሰራጭቷል ብለዋል።

በሥርጭት ሂደቱ ባለሥልጣኑ ከግብርና ቢሮ እና ከአርሶ አደሮች ጋር በተቀናጀ መንገድ መሥራት በመቻሉ አልፎ አልፎ በጸጥታ ምክንያት ከተፈጠሩ ችግሮች ውጭ የጎላ ችግር አለመከሰቱን ገልጸዋል። በቀጣይም የአፈር ማዳበሪያ ቀድሞ ወደ ዩኒየኖች እንደደረሰ በፍጥነት ወደ አርሶ አደሮች ለማድረስ ዝግጅት መደረጉን አቶ ጌትነት ገልጸዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበጎንደር ቀጣና የሁሉም ዞኖች ተወካይ ተፅዕኖ ፈጣሪ የሕብረተሰብ ክፍሎች የተሳተፉበት የሰላም ኮንፈረንስ ተካሄደ።
Next articleበምሥራቅ ጎጃም ዞን 107 ሚሊየን ችግኝ በወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት ለማስተከል ታቅዷል፡፡