
ባሕር ዳር: ሰኔ 13/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የሕጻናት ማቆያ መሠራቱ ሕጻናት ያሏቸው ሠራተኞች ቀልባቸውን ሰብስበው ሥራቸው ላይ እንዲያተኩሩ እንደሚያደርግ የአማራ ሥራ አመራር ኢንስቲትዩት የትምህርት እና ሥልጠና ምክትል ፕሬዚዳንት ሰብስበው አጥቃው (ዶ.ር) ተናግረዋል። ከዚህ ባሻገርም ሠራተኞች ልጆቻቸውን በቅርብ ኾነው መንከባከብ ሥለሚያስችላቸው ድርብ ፋይዳ አለው ነው ያሉት።
የሕጻናት ማቆያው በሌላ በኩል ምቹ የሥራ አካባቢን ስለሚፈጥር ሠራተኛውን የማነሳሳት እና የማትጋት አቅሙም ከፍተኛ ነው ብለዋል ምክትል ፕሬዚዳንቱ። ኢንስቲትዩቱ ሠርቶ ለአገልግሎት ክፍት ያደረገው የሕጻናት ማቆያ ሰባት ክፍሎችን የያዘ መኾኑም ተገልጿል። ለሕጻናቱ የመኝታ፣ የመጫዎቻ፣ የማብሰያ፣ የመመገቢያ እና የመጀመሪያ የሕክምና አገልግሎትን መስጫ ክፍሎች ያሉት ነው ብለዋል ።
በቀጣይም ሕጻናቱ የሚጫዎቱባቸው ልዩ ልዩ ዓይነ ግቡ ግብዓቶችን ለማሟላት በእቅድ ተይዘዋል ያሉት ዶክተር ሰብስበው አረንጓዴ ሥፍራም ይዘጋጃል ነው ያሉት። በአማራ ክልል ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ የሕጻናት መብት ደኅንነት ማስጠበቅ ዳይሬክተር አሻግሬ ዘውዴ ተቋማት የሕጻናት ማቆያ ባለመሥራታቸው በርካታ ሠራተኞች (ወላጆች) ልጃቸውን በቅርብ ኾነው ለመንከባከብ ሲሉ ከሥራ ገበታቸው ይቀራሉ፤ ይንገላታሉ ብለዋል። ሠራተኞች ሥራቸውን ቢወዱትም ይለቃሉ፤ ስለኾነም ኢንስቲትዩቱ ሠርቶ ለአገልግሎት ክፍት ያደረገው ማቆያ ለወላጅም ለተቋምም ከፍተኛ ጥቅም ያስገኛል ብለዋል።
የኢንስቲትዩቱ ሥራ ለሌሎች ተቋማት አርዓያነቱ ከፍተኛ ነው ብለዋል ዳይሬክተሩ። ከክልል እስከ ወረዳ ድረስ ያለው የማቆያ ብዛት አነስተኛ በመኾኑ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልኾኑ ተቋማት፣ የጋራ የመኖሪያ መንደሮች እንዲሁም ሌሎችም የሕጻናት ማቆያ እንዲገነቡ ቢሯቸው የማግባባት ሥራ መጀመሩን ጠቁመዋል።
የአማራ ሥራ አመራር ኢንስቲትዩት ሠራተኛ የኾኑት ወይዘሮ ጥሩሰው በዜ “ካሁን በፊት ልጄን አዝዬ ነበር የምሠራው፤ በመኾኑም ተፈትኛለሁ። ከእንግዲህማ ልጄን በማቆያ አስገብቼ በቅርብ መንከባከብ ስለምችል ተደስቻለሁ” ብለዋል። ሌላዋ ሠራተኛ ወይዘሮ ዘውዲቱ ፈንታቢል “ልጄ ምን ኾኖ ይኾን? ብሎ መጨነቅን ስለሚያስቀር በሙሉ ልቤ ሥራዬ ላይ እንዳተኩር ያደርገኛል” ነው ያሉት።
ሁለቱም አስተያዬት ሰጪዎች የኢንስቲትዩቱን የሥራ ኅላፊዎች አመሥግነዋል። የአማራ ሥራ አመራር ኢንስቲትዩት ሠራተኞች፣ ተጋባዥ እንግዶች እና መሪዎች ሰለ ዓይን ብሌን ልገሳ ትምሕርታዊ ውይይትም አድርገዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!