
ባሕር ዳር: ሰኔ 13/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በውይይቱ “ከተረጅነት አስተሳሰብ ለመላቀቅና በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ” እንደ ሀገር በተጀመረው እንቅስቃሴ የመንግሥት ሠራተኛው እና አመራሩ ቅንጅታዊ አሠራሮችን በመከተል ለውጤታማነቱ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ ተገልጿል።
የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ወርቁ ኃይለመማርያም “ልመና እና ተረጂነትን ሊያስቀሩ የሚችሉ የሥራ ዕድሎችን በማመቻቸት እና ያሉ አማራጮችን ሁሉ በመጠቀም፣ ቁጭት እና እልህን ተላብሰን በመሥራት ተረጂነትንና ድህነትን ታሪክ ማድረግ ይጠብቅብናል” ብለዋል።
በመኾኑም በየደረጃው የሚገኙ የመንግሥት ሠራተኞች ቅንጅታዊ አሠራርን ተግባራዊ በማድረግ የሌማት ትሩፋት ሥራን አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባልም ነው ያሉት፡፡ የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ፈንታሁን ስጦታው በበኩላቸው “የተሟላና ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ፣ የሀገራችንን ሉዓላዊነቷን እና ክብሯን ለማስጠበቅ፣ የተረጂነትና የልመና አስተሳሰብን ለመቅረፍ፣ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥን የሞት ሽረት ጉዳይ በማድረግ ሁለተናዊ ብልጽግናን ማረጋገጥ ይገባል” ብለዋል።
በውይይት መድረኩ የተገኙት የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ እና መሬት መምሪያ ኀላፊ አላምረው አበረ ጠንካራ የሥራ ባሕል በመፍጠር፣ የቤተሰብ ምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ እና ከተረጂነት በመላቀቅ ልመናን የሚፀየፍ ትውልድ መፍጠር ይገባል ብለዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!