ምክር ቤቱ የቀረበለትን የብድር ስምምነት አጸደቀ፡፡

20

ባሕር ዳር: ሰኔ 13/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ33ኛ መደበኛ ሥብሠባው የቀረበለትን የ275 ሚሊዮን ዶላር የብድር ስምምነት አጽድቋል። ምክር ቤቱ በኢትዮጵያ እና በዓለም አቀፍ የልማት ማኅበር መካከል ለሁለተኛው የከተሞች የመጠጥ ውኃ አቅርቦት እና ሳኒቴሽን ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ የሚውለውን የብድር ስምምነት ከተወያየ በኋላ በአዋጅ ቁጥር 1335/2016 በሙሉ ድምጽ አጽድቋል፡፡

የብድር ስምምነቱን በማስመልከት በምክር ቤቱ የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ ቤልጅጌ ማብራሪያ አቀርበዋል፡፡ ተጠሪ ሚኒስትሩ በመጠጥ ውኃ እና ሳኒቴሽን ዘርፍ በተነደፉ ፖሊሲዎች ስትራቴጂዎች እና ፕሮግራሞች ውስጥ የንጹህ መጠጥ ውኃ አቅርቦት እና ሳኒቴሽን አገልግሎት በስፋት እና በጥራት ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ እንደሚገኝ አሰረድተዋል፡፡

ለሁለተኛው የከተሞች የመጠጥ ውኃ አቅርቦት እና ሳኒቴሽን ፕሮግራም ተቀርጾ ባለፉት ዓመታት ተግባራዊ ሲኾን እንደቆየ አቶ ተስፋዬ አስረድተዋል፡፡ በብድር ስምምነቱ የተነደፉ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ እና ያጋጠመውን የበጀት ክፍተት ለመሙላት የተደረገ ተጨማሪ የብድር ስምምነት እንደኾነ አስረድተዋል፡፡
ብድሩም በቀጣይ ሦስት ዓመታት ተግባራዊ የሚኾን እና በጅምር ላይ ያለው የሁለተኛው የከተሞች የመጠጥ ውኃ እና ሳኒቴሽን ፕሮጀክት ለማጠናከር የሚያግዝ እንደኾነ ሚኒስትሩ አብራርተዋል፡፡

ተጠሪ ሚኒስትሩ ብድሩ ከወለድ ነጻ እና ባንኩ በሚወስነው መሠረት ጥቅም ላይ ባልዋለው ብድር ላይ በዓመት እስከ 0 ነጥብ 5 በመቶ የሚደርስ የግዴታ ክፍያ ሊከፈልበት እንደሚችል ገልጸዋል፡፡ ባንኩ የብድሩን ገንዘብ በማሥተዳደር ረገድ ለሚሰጠው አገልግሎት እስከ 0 ነጥብ 75 በመቶ የአገልግሎት ክፍያ እንደሚከፈልበት እና ብድሩ የ6 ዓመት የችሮታ ጊዜን ጨምሮ በ38 ዓመታት ውስጥ ተከፍሎ እንደሚጠናቀቅ ነው ያስረዱት፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በማኅበራዊ ትስስር ገጹ እንዳለው የምክር ቤት አባላትም ብድሩ የማኅበረሰቡን የንፁህ መጠጥ ውኃ አቅርቦትን ለማሳለጥ ሊያግዝ የሚችል የብድር ስምምነት እንደኾነ ተናግረዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article1 ሺህ 061 የስድስተኛ ክፍል ተማሪዎች ክልል አቀፍ ፈተና እየወሰዱ መኾኑ የወልድያ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ።
Next articleበወልድያ ከተማ አሥተዳደር የስድስተኛ ክፍል ተማሪዎች ክልል አቀፍ ፈተና እየወሰዱ ነው።