“በክልሉ ከ4 ሺህ በላይ ትምህርት ቤቶች ከ170 ሺህ በላይ ተማሪዎች የመጀመሪያ ዙር ፈተና እየተፈተኑ ነው”ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር)

38

ባሕር ዳር: ሰኔ 13/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አሥተባባሪ እና የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር)፣ የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው፣ የትምህርት ቢሮ እና የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳድር ትምህርት መምሪያ የሥራ ኀላፊዎች በትምህርት ቤቶች ተገኝተው የፈተና ሂደቱን ተመልክተዋል።

በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር በሚገኙ 56 ትምህርት ቤቶች ከ5 ሺህ በላይ ተማሪዎች ፈተናውን እየወሰዱ እንደሚገኙ የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው ገልጸዋል። ተማሪዎቹ በሰላማዊ መንገድ ፈተናውን እየተፈተኑ መኾኑንም ነው የገለጹልን። የስምንተኛ ክፍል ክልል አቀፍ ፈተና በሰላማዊ መንገድ መጠናቀቁን ያነሱት ተቀዳሚ ከንቲባው የስድስተኛ ክፍል እና በቀጣይ የሚሰጠው የ12ኛ ክፍል ፈተና በሰላም እንዲጠናቀቅ ቅድመ ዝግጅት መደረጉንም ገልጸዋል።

በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ እና የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) እንዳሉት ተማሪዎች በተረጋጋ እና የፈተና ሥርዓቱ ባስቀመጠው አሠራር መሠረት ተማሪዎች ፈተናውን እየወሰዱ ይገኛል። ዶክተር ሙሉነሽ እንዳሉት የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በክልል ደረጃ ከሚሰጡት ፈተናዎች ውስጥ የ6ኛ ክፍል አንዱ ነው። በክልሉ ከ4 ሺህ በላይ ትምህርት ቤቶች ከ170 ሺህ በላይ ተማሪዎች የመጀመሪያ ዙር ፈተና እየተፈተኑ ነው። የሁለተኛውን ዙር የፈተና ሂደት በተመለከተ ቢሮው በቀጣይ መረጃ እንደሚሰጥ ነው የገለጹት።

ተማሪዎች በሰላም ተፈትነው እንዲያጠናቅቁ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ያሳሰቡት ዶክተር ሙሉነሽ በሐምሌ 2016 ዓ.ም መጀመሪያ ለሚሰጠው የ12ኛ ክፍል ፈተና ዝግጅት እየተደረገ መኾኑንም ገልጸዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየምሥራቅ ጎጃም ዞን ሕዝብ ያጣውን ሰላም እንዲያገኝ በቁርጠኝነት እየሠሩ መኾናቸውን የዞኑ መሪዎች ገለጹ።
Next articleየኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የአምራች ኢንዱስትሪው ችግሮች እንዲፈቱ እገዛ ማድረጉ ተጠቆመ፡፡