የምሥራቅ ጎጃም ዞን ሕዝብ ያጣውን ሰላም እንዲያገኝ በቁርጠኝነት እየሠሩ መኾናቸውን የዞኑ መሪዎች ገለጹ።

17

ባሕር ዳር: ሰኔ 13/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ከሀምሌ ወር መጨረሻ ጀምሮ የደብረ ማርቆስ ከተማን ጨምሮ በምሥራቅ ጎጃም ዞን የተከሰተው አለመረጋጋት እንዲያበቃ የዞኑ ነዋሪዎች ጥረዋል፣ ግጭቶች በይቅርታ እና በእርቅ እንዲፈቱም ጥረት አድርገዋል። አሁን አንጻራዊ ሰላም ተገኝቷል። ለተገኘው ሰላም የሕዝቡ ድርሻ ከፍተኛ መኾኑም ተገልጿል።

በዞኑ ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ የወረዳ አሥተዳዳሪዎች እና የክፍለ ከተማ ሥራ አሥፈጻሚዎች የታየው አንጻራዊ ሰላም በግጭት ምክንያት ተቀዛቅዘው እና ተቋርጠው የነበሩ የልማት ተግባራት እንዲንቃቁ እያደረገ መኾኑንም ገልጸዋል። አሚኮ ያነጋገራቸው የአዋበል ወረዳ ዋና አሥተዳዳሪ ይሄነው መስፍን በወረዳቸው አኹን ለታየው አንጻራዊ ሰላም የሃገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች ያሳዩት ቁርጠኝነት ታላቅ ነበር ብለዋል።

የእነብሴ ሳር ምድር ወረዳ ዋና አሥተዳዳሪ ወንዲፍራው ጀመረ በወረዳቸው የታየው አንጻራዊ ሰላም ዘላቂ እንዲኾን እና ግጭቱ በእርቅ እና በይቅርታ እንዲፈታ ሕዝቡን በማስተባበር በቁርጠኝነት እየሠሩ መኾናቸውን ተናግረዋል። በደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር የመንቆረር ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ታገለ ትዕዛዙ የከተማው ሕዝብ በግጭቱ ምክንያት እያሳለፈ ከሚገኘው ችግር በመላቀቅ የቀደመ ሰላማዊ እና የተረጋጋ ሕይወት እንዲመራ ሕግ እና ሥርዓት እንዲከበርለት ይፈልጋል ብለዋል። የክፍለ ከተማው የሥራ ኅላፊዎችም የሕዝቡን የሰላም እና የልማት ፍላጎት ለመመለስ በቁርጠኝነት እየሠራን ነው ብለዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleከ5 ሺህ በላይ ተማሪዎች የ6ኛ ክፍል ፈተና እየወሰዱ መኾኑን በአማራ ክልል የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን አስታወቀ።
Next article“በክልሉ ከ4 ሺህ በላይ ትምህርት ቤቶች ከ170 ሺህ በላይ ተማሪዎች የመጀመሪያ ዙር ፈተና እየተፈተኑ ነው”ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር)