“የአየር ንብረት ለወጥ የሚያስከትለውን ችግር በዓለም አቀፍ መድረክ አጉልቶ በማሳየት በኩል የምሁራን ሚና የጎላ ነው” የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ስዩም መኮንን

11

አዲስ አበባ: ሰኔ 12/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የፕላን እና ልማት ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ከተወጣጡ ምሁራን ጋር በኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳዮች ላይ የዩኒቨርሲቲዎች ተሳትፎ በሚል ርእሰ ጉዳይ አውደ ጥናት እያካሄደ ነው። በአውደ ጥናቱ መክፈቻ ላይ የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ስዩም መኮንን ኢትዮጵያን እየፈተኑ ካሉ መሠረታዊ ችግሮች አንዱ እና ቀዳሚው የአየር ንብረት ለውጥ ነው ብለዋል።

ሚኒስትር ዴኤታው ኢትዮጵያ ችግሩን መሠረት በማድረግ የልማት እቅዷን የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማትን መነሻ ማድረጓን ገልጸዋል። ለችግሩም በፖሊሲ ማዕቀፍ ተግባር ተኮር ምላሽ እየሰጠች እንደኾነ ገልጸዋል። አረንጓዴ አሻራ፣ የሌማት ትሩፋት፣ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ እና የታዳሽ ኢነርጂ ማስፋፊያ ሥራዎችን በማሳያነት አንስተዋል።

የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን ችግር በዓለም አቀፍ መድረክ አጉልቶ በማሳየት በኩል የምሁራን ሚና የጎላ እንደኾነ ተናግረዋል። አቶ ስዩም የዛሬው መድረክ የፕላን እና ልማት ሚኒስቴር ከከፍተኛ ተቋማት ጋር ያለውን ቅንጅታዊ ሥራ ለማጠናከር ነው ብለዋል።

ዘጋቢ፦ በለጠ ታረቀኝ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleስደተኝነት የጥቂት ሀገራት ችግር ብቻ አለመኾኑን መገንዘብ እንደሚገባ ተገለጸ።
Next articleሁርሶ የኮንቲንጀንት ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት መሠረታዊ ወታደሮችን እያስመረቀ ነው።