
ባሕር ዳር: ሰኔ 13/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የዓለም የስደተኞች ቀን ዛሬ ሲከበር ስደተኝነት የጥቂት ሀገራት ችግር ብቻ አለመኾኑን መገንዘብ እንደሚገባ ተገልጿል፡፡ በዓለም የሚገኝ የትኛውም ሀገር ስደተኝነትን የመቀበል ወይም የመፍጠር አጋጣሚ ይኖረዋል፡፡ ይህ እውነታም ስደተኞችን ሰብዓዊ በኾነ መንገድ ማክበር፣ መጠበቅ እና መንከባከብ እንደሚገባ ያስረዳል፡፡
የአፍሪካ ኅብረት የሃብት እጥረት እያለባቸው ድንበራቸውን ለስደተኞች ክፍት አድርገው የሚቀበሉ የአፍሪካ ሀገራትን አመሥግኗል፡፡ “ስደተኝነትን መርጠው አይደለም” በሚለው መልዕክቱ የአፍሪካ ኅብረት ዓለም ስደተኞችን በመልካም የምትቀበል እናድርጋት ብሏል፡፡ በቅርብ የተደረገ ጥናት በዓለም ላይ ስደተኞችን በብዛት የሚቀበሉ አምስት ሀገራትን ይፋ አድርጓል። በቅደም ተከተልም እንዲህ ተቀምጠዋል፦
1.ኢራን ከ3 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ ስደተኞችን በመቀበል ቀዳሚዋ ሀገር ናት፡፡ የኢራቅ፣ የኩዌት፣ የኡዝበኪስታን እና የፓኪሰታን ስደተኞች ወደ ሀገሪቱ በስፋት የሚገቡ ዜጎች ናቸው፡፡
2.ተርኪየ ከ3 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ ስደተኞችን የተቀበለች ሀገር ናት፡፡ አብዛኞቹ ስደተኞች ከሶርያ ሲኾኑ ቁጥራቸው ጥቂት የኢራቅ፣ ኢራን እና አፍጋኒስታን ስደተኞችም ናቸው።
3. ጀርመን ስደተኞችን የምትቀበል ሃብታሟ ሀገር ናት፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን በ2024 ያወጣው ሪፖርት እንደሚያሳየው ጀርመን 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ስደተኞችን ተቀብላለች፡፡ አብዛኞቹ (1 ሚሊዮን) የሚኾኑት ከዩክሬን የሚሄዱ ናቸው፡፡700 ሺህ የሚጠጉት ደግሞ የሶርያ ስደተኞች ሆነዋል። በመቶሺዎች የሚቆጠሩ የኢራቅ እና አፍጋኒስታን ስደተኞችም ይገኛሉ፡፡
4. ፓኪስታን ከ2 ሚሊዮን በላይ ስደተኞችን የተቀበለች ሀገር ስትኾን አብዛኞቹ ስደተኞች ከአፍጋኒስታን የሄዱ ናቸው፡፡
5. ኡጋንዳ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ስደተኞችን የምታስተናግድ ሀገር ነች፡፡ የሀገሪቱ ፖሊሲ አውጪዎች ኡጋንዳ ለስደተኞች የተመቸች ሀገር እንድትኾን ሰፊ የፖሊሲ ማሻሻዎችን አድርገዋል፡፡ አብዛኞቹ ስደተኞች ከደቡብ ሱዳን እና ከዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኦፍ ኮንጎ የሚሄዱ ናቸው፡፡
ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው ስደተኞችን በመቀበል ኢትዮጵያ በዓለም ጥሩ ስም ያላት ሲኾን ስደተኞችን ከሚቀበሉ ሀገራት ዝርዝር ውስጥ 10ኛዋ ሀገር አድርጎም አስቀምጧታል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!