
ባሕር ዳር: ሰኔ 12/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ የተመዘገበው ኢኮኖሚያዊ እድገት ቀጣይነት እንዲኖረው ምርትና ምርታማነትን የሚያሳድጉ ሥራዎችን መሥራት ትኩረት ተሰጥቶት የሚከናወን ተግባር መኾኑን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡
ሚኒስትሩ ዶክተር ለገሰ ቱሉ የመንግሥት የ2016 ዓ.ም የማክሮ ኢኮኖሚ አፈጻጸም ላይ ከአገልግሎቱ ሠራተኞች ጋር በተደረገ ውይይት ላይ እንደተናገሩት በ2016 ዓ.ም የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በ7 ነጥብ 9 እድገት ማሳየቱን አስታውሰዋል። እድገቱ ቀጣይነት እንዲኖረው ለማድረግ አሁን እየተተገበሩ ያሉ የተለያዩ ኢንሼቲቮች በከፍተኛ ሁኔታ ማደግ አለባቸው ብለዋል፡፡
በሁሉም ዘርፍ የኢኮኖሚ እድገቱ ቀጣይነት እንዲኖረው በግብርናው፣ በኢንዱስትሪው፣ በማእድን፣ በቱሪዝምና በቴክኖሎጂ ዘርፎች ላይ ተጠናክሮ ይሠራልም ብለዋል፡፡
ለኢኮኖሚ እድገቱ ሰላም ወሳኝ መኾኑን አንስተዋል። ሚኒስትሩ መንግሥት አሁን የጀመረውን ሰላምን የማረጋገጥ ሥራ በሁሉም አከባቢዎች በተሻለና በተጠናከረ ሁኔታ ተግባራዊ እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡
የመንግሥትን የ2016ዓ.ም የ10 ወራት የማክሮ ኢኮኖሚ አፈጻጸም ሪፖርት ለሠራተኞች ያቀረቡት የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ የፈረንጆቹ /2023-2024/ የዓለም አማካይ የኢኮኖሚ እድገት 3 ነጥብ 2 በመቶ ሲሆን የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ግን በ7 ነጥብ 9 በመቶ አድጓል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በአሁኑ ወቅት ከአፍሪካ 5ኛ ግዙፉ ኢኮኖሚ ሲሆን ከዓለም ደግሞ 57ኛ ላይ እንደኾነም ነው ያነሱት ሚኒስትር ዴኤታዋ። ይህንን በቀጣዮቹ ዓመታት የተሻለ ደረጃ ላይ ለማድረስ ይሠራል ብለዋል፡፡
በቀጣዮቹ ዓመታት የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርሙን ውጤታማነት በማረጋገጥ ትላልቅ ፕሮጀክቶችን ወደ ውጤት በማሸጋገር፣ የብሔራዊ ምክክሩን ውጤታማ በማድረግና የተሻለ ሰላምን በማረጋገጥ ኢኮኖሚው የበለጠ እድገት እንዲያስመዘግብ ይሠራል ብለዋል፡፡
በተጨማሪም በቀጣዩ ዓመት አጠቃላይ ኢኮኖሚው በ8 ነጥብ 3 በመቶ እድገት እንዲያመጣ እንደሚሠራ ሰላማዊት ካሳ ጠቁመዋል። በዚህም ግብርናው 6 ነጥብ 1 በመቶ ፣ኢንዱስትሪው 2 ነጥብ 8 በመቶ እንዲሁም የአገልግሎት ዘርፉ 7 ነጥብ 1 በመቶ ድርሻ ይኖራቸዋል ነው ያሉት፡፡ የዋጋ ግሽበቱም አሁን ካለበት 25 ነጥብ 5 በመቶ ወደ 12 በመቶ ለማውረድ እንደሚሠራ መናገራቸውን ከመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች አገልግሎት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ሚኒስትር ዴኤታዋ ይህንን ውጤት ለማምጣት በሥራ ፈጠራ ከፍተኛ ሥራዎችን ለመሥራት መታቀዱን በመግለፅ በውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት 700 ሺህ ዜጎች እንዲሁም በሀገር ውስጥ ለ4 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር መታቀዱን ተናግረዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!