
እንጅባራ: ሰኔ 12/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ከፍተኛ መሪዎች በከተማ አሥተዳደሩ እየተሠሩ ያሉ የኢንቨስትመንት እና የመሠረተ ልማት ሥራዎችን ጎብኝተዋል። በጉብኝቱ የእንጅባራ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ የኔዓለም ዋሴ በከተማዋ እየተከናወኑ ባሉ የኢንቨስትመንት እና የመሠረተ ልማት ግንባታዎች ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው እንጅባራ ከተማን ለነዋሪዎች ምቹ እና ለኑሮ ተስማሚ ለማድረግ ከ32 ሚሊዮን ብር በላይ በሚኾን ወጪ የተለያዩ የመሠረተ ልማት ሥራዎች እየተሠሩ ነው ብለዋል። የመንገድ አካፋዮች ልማት፣ የጎርፍ ማፋሰሻ ዲች ግንባታ እና የሕዝብ መድኃኒት ቤት በግንባታ ሂደት ላይ ከሚገኙ መሠረተ ልማቶች መካከል እንደሚገኙበትም ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው አንስተዋል።
እንጅባራ ከተማ በፈጣን የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ላይ እንደምትገኝ የገለጹት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ለዚህም የግል ባለሀብቶች ተሳትፎ የጎላ እንደኾነ ተናግረዋል።
ዘጋቢ፦ ሳሙኤል አማረ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!