
ደሴ: ሰኔ 12/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶች ኤግዚቢሽን እና ባዛር በደሴ ከተማ ተከፍቷል፡፡
በአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ አስተባባሪነት የደቡብ ወሎ ዞን፣ የኮምቦልቻ እና ደሴ ከተማ አሥተዳደር ንግድ እና ገበያ ልማት መምሪያዎች በቅንጅት ገበያውን ለማረጋጋት በደሴ ከተማ ኤግዚቢሽን እና ባዛርን አስጀምረዋል፡፡አሚኮ ያነጋገራቸው የባዛሩ አዘጋጆች በ2016 ዓ.ም “የኢትዮጵያን ይግዙ” በሚል መሪ መልዕክት የሚከበረውን የንግድ ቀን ምክንያት በማድረግ ማኅበረሰቡን እና አቅራቢውን ተጠቃሚ የሚያደርግ ሥራ መሠራቱን ጠቁመዋል፡፡ ባዛሩ ኅብረተሰቡ የሚፈልገውን ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኝ ያስችለዋልም ብለዋል፡፡
የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ኀላፊ ኢብራሂም መሐመድ (ዶ.ር) እንደ ሀገር አሁን ላይ ካለው የኑሮ ውድነት አንጻር ንግዱን እና ግብይቱን ጤናማ በማድረግ የኑሮ ውድነቱን ማረጋጋት ወቅቱ የሚጠይቀው ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡
በደቡብ ወሎ ዞን ደሴ ከተማ እና ኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ንግድ መምሪያዎች በጋራ በመኾን ያስጀመሩት የገበያ ማረጋጋት ሥራ በሌሎችም አካባቢዎች ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ነው ያሉት፡፡ ቢሮ ኀላፊው በቀጣይም በክልሉ የገበያ ትስስርን የሚፈጥሩ የገበያ ማዕከላትን በማስፋት በከተማ አሥተዳደሮች በሁለት ወር በከተሞች ደግሞ በሦስት ወር አንድ ጊዜ ኢግዚቢሽን እና ባዛር ይዘጋጃልም ብለዋል፡፡ በደሴ ከተማ የቀድሞው መናኸሪያ የተጀመረው ኢግዚቢሽን እና ባዛር ከሰኔ 12/2016 ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታይ አምስት ቀናት ቆይታ እንደሚኖረው ተጠቁሟል፡፡
ዘጋቢ፡- ማህሌት ተፈራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!